ቀጥታ፡

በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና ለመሳተፍ ከ155 ሺህ በላይ ሰዎች ተመዝግበዋል- የኢትዮጵያ ልማት ባንክ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 18/2015 በአራተኛው ዙር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና ለመሳተፍ እስከ አሁን ከ155 ሺህ በላይ ሰዎች መመዝባቸውን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አስታወቀ።

ምዝገባው እስከ ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም እንደሚቆይ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የሚዲያ እና ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ያብስራ ከበደ የስልጠናው ምዝገባ መቐለ እና ሽሬን ጨምሮ ከ25 በላይ በሚሆኑ ከተሞች እየተካሄደ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከ50 እስከ 60 ሺህ ሰዎችን ለመመዝገብ ታስቦ እስከ አሁን ከ155 ሺህ በላይ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች መመዝገባቸውን አመልክተዋል።

የተመዝጋቢዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን በመጠቆም።

ወረፋ በመያዝ ገንዘብ ለመቀበል የሚሞክሩ አካላት መኖራቸውንና ልማት ባንክ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና አዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ያብስራ ገለጻ፤ ተመዝጋቢዎች ወረፋ በማስያዝ ገንዘብ ከሚቀበሉ ሰዎች መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል።

በ4ኛው ዙር የስልጠናው የምዝገባ የጊዜ ገደብ ቢጠናቀቅም ያለውን ፍላጎት ታሳቢ በማድረግ እስከ እሁድ ጥር 21 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም ተደርጓል።

በተያዘው የጊዜ ገደብ መመዝገብ ያልቻሉ አካላትም በቀጣይ ሰኔ ወር 2015 ዓ.ም በሚጀመረው 5ኛው ዙር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና በመመዝገብ መሳተፍ እንደሚችሉ አቶ ያብስራ ጠቁመዋል።

ስልጠናው ለኢንተርፕራይዞቹ የስራ እድል በመፍጠር፣በቴክኖሎጂ ሽግግር እና ገበያን በማረጋጋት ረገድ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም