ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሚርጃና ስፖልጃሪክ ኤገርን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይታቸው አቶ ደመቀ መኮንን መንግሥት የሰላም ስምምነቱን በቁርጠኝነት እየተገበረ መሆኑን ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅትም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ምክንያት ተቋርጠው የነበሩ መሠረታዊ አገልግሎቶች በተጠናከረ መልኩ አገልግሎት እንዲጀምሩ እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነትንም የማስፋፋት እና የማጠናከር ተግባራት እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

በግጭቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ የመግንባት እና የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ሁሉን አቀፍ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኀበር ኮሚቴ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ አጋር አካላትም እስካሁን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል ተፈጥሮ በነበረው ግጭት እና በድርቅ ምክንያት እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ወገኖችን ተደራሽ ለማድረግ መንግሥት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ገልፀዋል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ሚርጃና ስፖልጃሪክ ኤገር በበኩላቸው ማኅበሩ በኢትዮጵያ የሚሰጠውን ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቷ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ሁኔታ ተስፋ ሰጭ መሆኑንም ገልጸዋል።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ኮሚቴ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች ሰብአዊ እርዳታ ለሚሹ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ በማስፋት አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል-አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም