ሞሮኮ ከኢትዮጵያ ጋር በባህል እና ስፖርት መስክ ያላትን ትብብር ማጠናከር እንደምትሻ ገለጸች

103

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 ሞሮኮ ከኢትዮጵያ ጋር በባህል እና ስፖርት መስክ ያላትን ትብብር ማጠናከር እንደምትፈልግ አስታወቀች።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ኒዝሃ አለዊ መሐመዲ ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ በእግር ኳስና አትሌቲክስ የልምድ እና የእውቀት ልውጥጥ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉን አቶ ቀጄላ ገልጸዋል።

በተለይም ሞሮኮ በእግር ኳስ አካዳሚዋ ያላትን ልምድ እና በአትሌቲክስ በሴቶች ያላትን ውጤታማነቷን የተመለከተ ልምድ እንድታካፍል ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የሞሮኮ አምባሳደር ኒዝሃ አለዊ መሐመዲ ሁለቱ አገራት በባህል፣ በኪነ ጥበብና ስፖርት መስክ በትብብር ለመስራትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከዚህ ቀደም ለመፈራረም ያዘጋጁት ሰነድ ላይ ማሻሻያ በማድረግ ስምምነቱ እንዲፈረም ጠይቀዋል።

የስምምነቱ መፈረም በተጠቀሱት መስኮች ያለውን የአገራቱን ትብብር እንደሚያጎለብት አመልክተዋል።

አምባሳደር ኒዝሃ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ ሞሮኮን እንዲጎበኙ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ቃል ገብተዋል።

በተጨማሪም በኳታር አስተናጋጅነት በተካሄደው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ኢትዮጵያ በውድድሩ አራተኛ ደረጃን ይዛ ላጠናቀቀችው ሞሮኮ ላሳዩት ድጋፍ አምባሳደሯ ምስጋና ማቅረባቸውን ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም