ህብረብሔራዊ አንድነታችንንና ሰላማችንን ጠብቀን ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሁላችንም በትጋት መስራት አለብን-አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ

ጅግጅጋ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 ህብረብሔራዊ አንድነታችንንና ሰላማችንን ጠብቀን የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁላችንም ተባብረንና ተቻችለን በትጋት መስራት አለብን ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለአቅመ ደካሞች የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች ዛሬ ለተጠቃሚዎች በተላለፉበት ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ባደረጉት ንግግር፤ ሰላማችንን ለማረጋገጥ የምንሰራውን ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ወንድማማችነትን አጎልብተን በፍቅርና በአንድነት አብርን በመቆም ጠንክረን መስራት አለብን ሲሉም ገልጸዋል።

በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለአረጋውያንና አቅመ ደካሞች ምቹ መኖሪያ እንዲያገኙ መደረጉ እርስ በእርስ ከተጋገዝን የማንሻገራው ችግር እንደማይኖር ማሳያ ነው" ብለዋል።

ሁላችንም ተግተን ከሰራን ኢትዮጵያን ማበልፀግ በእጃችን ያለ ጉዳይ ነው ያሉት አፈ- ጉባኤው እዚህ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ያለው መነቃቃት የሚያመለክተውም ይሄው ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ህብረብሔራዊ አንድነታችንንና ሰላማችንን ጠብቀን የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ ሁላችንም ተባብረንና ተቻችለን በትጋት መስራት አለብን ሲሉ ገልጸዋል። 

ጠንክረን ከሰራን ልማታችን እውን እናደርጋለን፤ የእድገት ጉዟችንን እናሳካለን፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን ትለወጣለች፤ ትሻጋራለች፤ ህዝቡም በፍቅር በአንድነት ይቆማል ብለዋል አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በንግግራቸው።

ምናልባት የዛፍ እና ከቤት ውጪ ምስል

በጅግጂጋ ከተማ ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከለውጡ በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያስጀመሯቸው በርካታ ስራዎች የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ የሚያፋጥኑ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።  

በጅግጅጋ ከተማ የአቅመ ደካሞች ቤቶችን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአዲስ መልክ መገንባት መቻላቸው የዚሁ አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ለግንባታው አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም አመስግነዋል።  

በቀጣይም የክልሉ መንግስት ባለሀብቶችን፣ ዳያስፖራዎችንና ሌሎችም አቅም ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባባር በተመሳሳይ መልኩ በጅግጂጋ ከተማ ሃምሳ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለመገንባት ማቀዳቸውን አስታውቀዋል።  

በሌሎች የክልሉ ዞኖችና ከተሞችም በተመሳሳይ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

መኖሪያ ቤቶቹ የተገነቡት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተጠሪ ተቋማትና ከክልሉ መንግስት በተመደበ 20 ሚሊዮን ብር መሆኑን የገለጹት ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ፀሐፊ ዶክተር ምሥራቅ መኮንን ናቸው። 

የእነዚህ 31 መኖሪያ ቤቶች ቁልፍም ተጠቃሚዎች ተረክበዋል። 

በአዲስ መልክ ተገንብተው ቁልፉን የተረከቡ ተጠቃሚዎች ለመፍረስ የተቃረበ ከደሳሳ ቤት ወጥተው አዲስ ቤት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል። 

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ በዶ ተገኝተዋል። 

ምናልባት የ9 ሰዎች፤ የቆሙ ሰዎች እና ከቤት ውጪ ምስል

በቤቶቹ ግንባታ የተሳተፉት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ተጠሪ ተቋማት በሆኑት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መሆናቸው ታውቋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በጅግጀጋ ከተማ በመገንባት ላይ ያለው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ህንፃን ጎብኝተዋል።

ግንባታው 76 በመቶ የደረሰው ህንፃው የመሰብሰቢያ አደራሽን ጨምሮ የተለያዩ መገልገያዎችን ማካተቱንና ከአራት ወር በኋላ እንደሚጠናቀቅ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም