"የሲዳማ ብሔራዊ አርነት ግንባር" ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደአገር ገባ - ኢዜአ አማርኛ
"የሲዳማ ብሔራዊ አርነት ግንባር" ሰላማዊ ትግል ለማድረግ ወደአገር ገባ
አዲስ አበባ መስከረም 24/2011 በውጭ አገር ሆኖ የፖለቲካ ትግል ሲያደርግ የነበረው "የሲዳማ ብሔራዊ አርነት ግንባር" በሚል የሚጠራው ቡድን ዛሬ ወደአገር ቤት ተመለሰ። የቡድኑ አመራር አባላት ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ሲገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎችና በአገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል በማድረግ ላይ የሚገኘው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ የሥራ ኃላፊዎች ተቀብለዋቸዋል። ቡድኑ ወደኢትዮጵያ የተመለሰው በአገሪቱ የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ በተደረገው ጥሪ መሰረት ትግሉን በሰላማዊ መንገድ ለመቀጠል በመወሰን መሆኑን የግንባሩ ውጭ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደንባቦ ናቴ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ኃላፊው አክለውም "ግንባሩ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከመላው የአገሪቱ ህዝቦች ጋር በመተባበር አገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት በሰላማዊ ትግል የድርሻችንን እንወጣለን" ብለዋል። የሲዳማ ህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ትግሉን በሰላማዊ መንገድ የሚቀጥሉ መሆኑን ነው አቶ ደንባቦ ያመለከቱት። ግንባሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረው ለውጥ የፈጠራቸውን ተስፋዎች በመጠቀም "መብቱ የተከበረና በማንነቱ የሚኮራ የሲዳማ ህዝብን እውን ለማድረግ በርትቶ ይሰራል" ብለዋል። ከዚህ ባሻገርም ግንባሩ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጎን በመቆም ለአገሪቱ የወደፊት ዕድገት የድርሻውን ለመወጣት መዘጋጀቱን አቶ ደንባቦ ገልፀዋል። ለቡድኑ አቀባበል ያደጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ከወራት በፊት ባደረገው ጥሪ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ገብተው ሰላማዊ ትግል ጀምረዋል። የሲዳማ ብሔራዊ አርነት ግንባርም ጥሪውን ተቀብሎ ወደ አገር መግባቱን በማድነቅ ''ግንባሩ አገሪቱ በምታካሂዳቸው የዴሞክራሲና የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ የድርሻውን ለመወጣት ይተጋል'' የሚል እምነት እንዳላቸው ገልፀዋል። በአገር ውስጥ ሰላማዊ ትግል በማድረግ ላይ የሚገኘው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ሊቀመንበር አቶ ዱካለ ላሜሱ ፓርቲያቸው ወደአገሩ ከተመለሰው የሲዳማ ብሔራዊ አርነት ግንባር ጋር በጋራ ለመስራት እንደሚፈልግ ተናግረዋል። የፓርቲዎቹ ስትራቴጂና ፕሮግራም ተመሳሳይነት ያለው በመሆኑ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ሁኔታ እንደሚፈጥር ጠቁመዋል። የሲዳማ ብሔራዊ አርነት ግንባር የሲዳማ አርነት ንቅናቄን ጨምሮ በአገሪቱ ከሚገኙ ሌሎች ፓርቲዎችም ጋር ተባብረው ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አመራሮቹ ገልፀዋል። ዛሬ አዲስ አበባ የገቡት የሲዳማ ብሔራዊ አርነት ግንባር ምክትል ሊቀመንበር ፉቴ ሙሱ፣ የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ሓላፊ አቶ ደንባቦ ናቴ እና ሌሎች የግንባሩ የሥራ አስፈፃሚ አባላት ናቸው። የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ቤታና ወጤሶ በህክምና ጉዳይ ምክንያት እንዳልመጡ የተጠቀሰ ሲሆን ህክምናቸውን ሲጨርሱ ወደአገራቸው እንደሚመጡ የግንባሩ አመራሮች ለኢዜአ ገልፀዋል።