በሲዳማ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ላይ በማተኮር እየተሰራ ነው - አቶ ደስታ ሌዳሞ

114

ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 በሲዳማ ክልል የትምህርት ጥራትን ለማምጣት በዋናነት በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ተደራሽነትና ብቃት ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

በክልሉ ሸበዲኖ ወረዳ አንድ ባለሀብት ያስገነቡትን ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ዛሬ ለክልሉ መንግስት አስረክበዋል።

በርክክብና ምረቃት ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንደተናገሩት በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማምጣት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል።

በተለይም የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ምቹ የማድረግና ማብቃት ላይ ክልሉ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በትምህርት ስራ ላይ የክልሉ ህዝብ ተሳትፎ ወሳኝ በመሆኑ ባለሀብቱን፣ የመንግስት ሰራተኛና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ ወደ ስራ መገባቱንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

“በዚህም የሲዳማ ክልል የትምህርት ተሀድሶ መርሀ-ግብር በማዘጋጀት ከባለሀብቱና ከመንግስት ሰራተኛው ጋር ውይይት በማድረግ በዋናነት የቅድመ መደበኛ ትምህርትን በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው” ብለዋል።

ይህም ክልሉን በትምህርት ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ሲሆን የነበሩ ስብራቶችና ክፍተቶችን የሚጠግን መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ላይ በማተኮር የተጀመረው ስራ ውጤት እያመጣ እንደሚገኝ ገልጸው ለአብነትም ባለሀብቱን በማሳተፍ በእያንዳንዱ ቀበሌ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን የመገንባት ስራ እየተካሄደ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ በየነ በራሶ በበኩላቸው የክልሉን የትምህርት ተደራሽነትና ጥራት በማስፋት ብቁና በክህሎት የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ታቅዶ ወደ ትግበራ ተገብቷል።

“የትምህርት ስርዓቱ በከተማና በገጠር ፍትሀዋኒነት የጎደለው በመሆኑ በከተሞች ያለውን ሁኔታ በክልሉ ገጠር አካባቢዎች በማምጣት የማመጣጠን ስራ በመስራት ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ተደራሽ እናደርጋለን” ብለዋል።

በተለያዩ መስኮች በክልሉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን በማነጋገር ከሶስት መቶ በላይ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በተያዘው ዕቅድ መሰረት በርካቶች ቦታ ተረክበው ግንባታ መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ትምህርት ቤቱን ገንብተው በማጠናቀቅ ለክልሉ መንግስት ያስረከቡት ባለሀብቱ አቶ ዱካሌ ዋቀዮ በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንዳሉት የልማት ስራ የመንግስት ብቻ አድርጎ መውሰድ አይገባም።

በተለይም ትምህርት ላይ የሚደረግ ተሳትፎ ደግሞ ሀገርንና አካባቢን መገንባት መሆኑን ገልጸው ባደረጉት አስተዋጽኦ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከአራት ወራት በፊት በሸበዲኖ ወረዳ ቦኖያ ሚሪዴ ቀበሌ በተረከቡት ቦታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግንባታውን በማጠናቀቅ ከተሟላ የትምህርት ቁሳቁስ ጋር ትምህርት ቤቱን ማስረከባቸውን ገልጸዋል።

ዛሬ በባለሀብቱ ተገንብቶ የተመረቀውና ርክክብ የተደረገው ትምህርት ቤት 210 የቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ጀምሯል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የክልልና የወረዳ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም