በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በባህር ትራንስፖርት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን በላይ ዕቃ ማጓጓዝ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በባህር ትራንስፖርት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን በላይ ዕቃ ማጓጓዝ ተችሏል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት በባህር ትራንስፖርት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን በላይ ዕቃ በማጓጓዝ ከእቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሮባ መገርሳ፤ የድርጅቱን የስድስት ወራት ክንውን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በበጀት ዓመቱ አጋማሽ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን የኦፕሬሽን አገልግሎት መስጠቱን ገልጸዋል።
በግማሽ ዓመቱ በመርከብ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን በላይ ዕቃ ለማጓጓዝ ታቅዶ እንደነበር አስታውሰው የመዘገበው ስኬት ከእቅዱ በላይ መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም በድርጅቱ መርከቦችና የኪራይ መርከቦችን በመጠቀም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ቶን በላይ ዕቃ በማጓጓዝ ከእቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም 312 ሺህ ቶን ብትን እንዲሁም 4 ሺህ 500 በኮንቴይነር የታሸገ ጭነት መጓጓዙን ተናግረው በኮንቴይነር ከተጓጓዙት ጭነቶች መካከል 3 ሺህ 79 በአገር ውስጥ መታሸጉንም ጠቁመዋል።
በአገር ውስጥ የሚታሸገው የወጪ ጭነት እየጨመረ በመምጣቱ ለዚህ አገልግሎት ይወጣ የነበረውን ወጪ ማስቀረት መቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
የኮንቴይነር የጅቡቲ ወደብ ቆይታንም በመቀነስ በአጠቃላይ በስድስት ወራቱ 19 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።
የድርጅቱን የጭነት ተሽከርካሪዎች የመጫን አቅም ለማሳደግ፣ ያረጁ ተሽከርካሪዎችን ከስምሪት ለማስወጣት በተሰራው ስራም የ185 የተሽከርካሪዎች ግዢ መፈጸሙንም ገልጸዋል፡፡
በድርጅቱ መርከቦች ጭነት የማንሳት አቅምን ለማሳደግ በተሰራው ስራም ከዚህ በፊት ከነበሩት መርከቦች በተጨማሪ የሁለት መርከቦች ግዥ በሂደት እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የድርጅቱን መርከቦች በቅብብሎሽ ንግድ በማሰማራትም የላቀ ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው፣ የድርጅቱን መርከቦች ትርፋማነት ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል።
ድርጅቱ በስድስት ወራት ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ የማህበራዊ አገልግሎት ተግባራትን አከናውኗል ተብሏል።