የእስራኤል እና ኢትዮጵያ የግብርና እና የቴክኖሎጂ ልማት ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - በኢትዮጵያ የእሰራኤል አምባሳደር - ኢዜአ አማርኛ
የእስራኤል እና ኢትዮጵያ የግብርና እና የቴክኖሎጂ ልማት ትብብር ተጠናክሮ ይቀጥላል - በኢትዮጵያ የእሰራኤል አምባሳደር
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 እስራኤል በግብርና እና ቴክኖሎጂ ልማት ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር አጠናክራ የምትቀጥል መሆኑን በኢትዮጵያ የእሰራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የእሰራኤል አምባሳደር አለልኝ አድማሱ፤ የኢትዮ-እስራኤልን የሁለትዮሽ ግንኙነትና የልማት ትብብር በተመለከተ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
አምባሰደሩ እንዳሉትም እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር በተለይም በንግድ፣ኢንቨስትመንት፣ በህዝብ ለህዝብ እና በባህል ጭምር የቆየ ጠንካራ ወዳጅነት አላቸው።
የሁለቱ አገሮች ግንኙነት አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጠቅሰው በግብርና፣ ቴክኖሎጂ፣ በኢቪየሽንና ሌሎችም ዘርፎች ተቀራርበው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም እስራኤል የልማት ትብብርን ጨምሮ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት እንደምትደግፍ አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።
እስራኤል በኢትዮጵያ በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች የገንዘብ፣ አልባሳትና ሌሎችንም ድጋፎች ማድረጓን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።
በግብርና፣ ቴክኖሎጂና ሌሎችም ዘርፎች የተሰማሩ የእስራኤል ባለሃብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በተለይም በበጋ መስኖ የስንዴ ምርት ያሳየችውን እመርታ አድንቀው ግብርናውን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እስራኤል እገዛ ታደርጋለች ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በማስረዳት የእስራኤል ባለሃብቶች በግብርና፣ ቴክኖሎጂና ሌሎችም ዘርፎች የመሰማራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በጤናው ዘርፍም በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ከሚገኙ የጤና ተቋማት ጋር በልምድ ልውውጥ፣ በልብ ህክምና እና ሌሎች ዘርፎች በትብብር እንሰራለን ብለዋል።
እስራኤል በታዳሽ ሃይል ያላትን ተሞክሮ ለማካፈል ባሳየችው ፍላጎት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአቬየሽን ዘርፍም በኤሮስፔስ ከአፍሪካ ተጠቃሽ ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የሁለቱ ሀገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ጠንካራ መሆኑን ያስታወሱት አምባሳደሩ የጥምቀት በዓልን ለመታደም ከእስራኤል ከ7 ሺህ በላይ ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያና እስራኤል ግንኙነት ከንግስተ ሳባና ከንጉስ ሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እስካሁን የዘለቀ ሲሆን እኤአ በ1992 በአዲስ መልክ የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን ማደሳቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።