በጅግጅጋ ከተማ ለአቅመ ደካሞች የተገነቡ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላለፉ - ኢዜአ አማርኛ
በጅግጅጋ ከተማ ለአቅመ ደካሞች የተገነቡ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ተላለፉ
ጅግጅጋ(ኢዜአ) ጥር 17 ቀን 2015 በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ለአቅመ ደካሞች የተገነቡ መኖሪያ ቤቶች ዛሬ ለተጠቃሚዎች ተላለፉ ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎና የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በተገኙበት የተላለፉት መኖሪያ ቤቶቹ 31 ሲሆኑ፤ የቤቶቹን ቁልፍም ተጠቃሚዎች ተረክበዋል።
መኖሪያ ቤቶቹ የተገነቡት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተጠሪ ተቋማቱና ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት መሆኑን በርክክቡ ስነ-ሰርዓት ላይ ተገልጿል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በወቅቱ "ለአረጋውያንና አቅመ ደካሞች ምቹ መኖሪያ እንዲያገኙ መደረጉ እርስ በእርስ ከተጋገዝን የማንሻገረው ችግር እንደማይኖር ማሳያ ነው" ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ሙስጠፌ ሙሁመድ በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከለውጡ በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያስጀመሯቸው በርካታ ስራዎች የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ የሚያፋጥኑ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
በጅግጅጋ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ቤቶችን በበጎ ፍቃድ አገልግሎት በአዲስ መልክ መገንባት መቻላቸው የዚሁ አንዱ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ለግንባታው አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በቀጣይም የክልሉ መንግስትም በተመሳሳይ መልኩ ሃምሳ የአቅመ ደካማ ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱንም አስታውቀዋል።
ለቤቶቹ ግንባታ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስራ ስድስት ሚሊየን ብር፣ ከተጠሪ ተቋማት አራት ሚሊየን ብርና ከክልሉ መንግስት አስር ሚሊየን ብር ውጪ መደረጉም ተመልክቷል።
በአዲስ መልክ ተገንብቶ የተጠናቀቁ ቤቶች ተጠቃሚ የሆኑ እድለኞች ለመፍረስ የተቃረበ ደሳሳ ቤት ወጥተው አዲስ ቤት በማግኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በበጎ ፈቃድ ስራው ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ተጠሪ ተቋማት በሆኑ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ፣የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣንና የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መሆናቸው ታውቋል።