ቀጥታ፡

ጥርን በባህርዳር በሚል መርሃ ግብር የሚካሄዱ ኩነቶች የበለጠ ሊተዋወቁ ይገባል - ታዳሚዎች

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥር 17/2015 ጥርን በባህርዳር በሚል የሚካሄዱ ልዩ ልዩ ሁነቶች የቱሪስቶችን ቀልብ የሚስቡ በመሆናቸው በማልማቱና በማስተዋወቁ ረገድ የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባ የሁነቱ ተሳታፊዎች ገለጹ።

የጥርን በባህር ዳር አንዱ መርሃ ግብር የሆነው የታንኳ ቀዘፋ ውድድርና የጀልባ ትርኢት ትናንት ማምሻውን በጣና ኃይቅ ላይ ተካሂዷል።

ከአዲስ አበባ በመምጣት በፕሮግራሙ የታደመው ጋዜጠኛና ደራሲ ሄኖክ ስዩም ለኢዜአ እንደገለፀው ኢትዮጵያ ታይተው የማይጠገቡ የበርካታ ቅርሶች፣ ታሪኮችና መስህቦች ባለቤት ናት። 

ባህር ዳር ከተማ ደግሞ የጣናን ኃይቅ ዳርቻና አባይን ተንተርሳ የተመሰረተች በመሆኗ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን አስችሏታል ብለዋል። 

በተለይም በጣና ኃይቅ ውስጥ በሚገኙ ደሴቶች ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶችን አቅፎ የያዘ ከመሆኑም በላይ በዓለም ረጅሙና ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የአባይ ወንዝ መገኛ ከተማ ጭምር ናት ብለዋል።  

በወርሃ ጥር በከተማዋ የሚከበሩ በርካታ በዓላት ከመኖራቸው ጋር ተያይዞም ጥርን በባህር ዳር በሚል መርሃ ግብር መከናወኑ ከተማዋን የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች በስፋት እንዲጎበኟት ዕድል እንደሚሰጣትም ጨምረው ገልጸዋል።  

በተለይም የታንኳ ቀዘፋ ውድድርና የጀልባ ትርኢቱ እንዲህ በአማረ መልኩ መከበር መጀመሩ ከተማዋ ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ምቹ መደላድል የሚፈጥር መሆኑንም አክለዋል። 

ባህር ዳር ድንቅ ለቱሪስት መስህቦች ያሏት በመሆኑም ጥርን በባህር ዳር በሚል መርሃግብር የሚከናወኑት ሁነቶች ላይ በርካታ እንግዳ እንዲሳተፍ ፕሮግራሙን ቀደም ብሎ በካሌንደር ጭምር ማስተዋወቅ እንደሚገባም ጋዜጠኛና ደራሲ ሄኖክ ጠቁሟል።

 ሌላኛዋ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪና የፎቶ ግራፍ ባለሙያ ሰላማዊት ቢያዝን በበኩሏ በምታነሳቸው ፎቶዎች የከተማዋን ገፅታና የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎችን እያስተዋወቀች እንደምትገኝ ገልጻለች። 

በተለይም ጥርን በባህር ዳር መርሃ ግብር ላይ የእግር ጉዞ፣ ሽርሽር በሳይክል፣ የታንኳ ቀዘፋ ውድድርና የጀልባ ትርኢት የመሳሰሉ ኩነቶችንና የመስህብ ስፍራዎችን ፎቶ በማንሳት ከተማዋ መልካም ገፅታ እንዲኖራት የማስተዋወቅ ስራ እየሰራች መሆኗን ገልጻለች። 

በግል የማህበራዊ ትስስር ገፅ የምትለጥፋቸውን ፎቶዎች ሰዎች በመመልከት እንደሚያበረታቷት ገልፃ፤ በቀጣይም በከተማዋ በጥር ወር የሚካሄዱ ፕሮግራሞችን በፎቶ በማስተዋወቅ ከተማዋ ዋነኛ የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን በትኩረት እንደምትሰራ ተናግራለች።  

ባህር ዳር ለቱሪስት መስህብነት በእጅጉ ተመራጭ እንደመሆኗ መጠን ጥርን በባህር ዳር የሚከበረው ፕሮግራም በርካታ እንግዳ እንዲሳተፍ ፕሮግራሙን በግልፅ ቀደም ብሎ ማስተዋወቅ እንደሚገባ ጠቁማለች። 

የፕሮግራሙ ተሳታፊ አቶ ሰሎሞን በለጠ በበኩላቸው ለቱሪዝም መስህብ ሊሆን የሚችለውን የታንኳ ቀዘፋ ውድድርና የጀልባ ትርኢት ሁሉም ሊያየውና ሊጎበኘው የሚገባ ድንቅ የመስህብ ሃብት ነው ብለዋል። 

ተፈጥሮ የቸራትን ከተማ ለመጎብኘት ጥርን በባህር ዳር የሚካሄዱ ፕሮግራሞችን ሁሉም አውቆ እንዲጎበኘው አቅማቸው በፈቀደው ልክ ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩ ገልጸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በዘርፉ ተግተው እንዲሰሩም ጠይቀዋል።  

በተካሄደው የታንኳ ቀዘፋ ውድድርና የጀልባ ትርኢት ከ70 በላይ ታንኳዎችና 60 የሚሆኑ ጀልባዎች ተሳትፈዋል።  

በታንኳ ቀዘፋ ውድድሩ በሴቶችና በወንዶች ከ1ኛ እስከ 3ኛ ለወጡ ተወዳዳሪዎች የማበረታቻ ሽልማት ተበርክቷል። 

በቀድሞው ጊዮን ሆቴል ዳርቻ በተካሄደው የታንኳ ቀዘፋና የጀልባዎች ትርኢት ላይ የተገኙት የከተማዋ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው፣ ከተማዋ በተፈጥሮ ያላትን የመስህብ ሃብት በመጠበቅና በማልማት የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች መዳረሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። 

በባህርዳር ከተማና አካባቢዋ ወደ 30 የሚደርሱ የቱሪስት መዳረሻዎች መኖራቸውም ተጠቅሷል። 

ይህ የታንኳ ቀዘፋና የጀልባ ትርኢት የዛሬ 6 ዓመት በ30 ታንኳና በ40 ጀልባዎች መጀመሩን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም