ጥንቃቄ የሚሻው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም - ኢዜአ አማርኛ
ጥንቃቄ የሚሻው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም
ምናሴ ያደሳ(ኢዜአ) እልኽኝነትና ብሽሽቅ ከመጥፎ አዕምሮ የሚመነጭ አገር አጥፊ አረም ነው ፡፡ በማሳ ውስጥ በሰብሎች መካከል ከተሰራጨ ለማጥፋት አንደሚያስቸግር አጥፊ አረም ፡፡ አረም አንዴ ከተስፋፋ ከሰብል ጋር ተደባልቆ እድሜ ልክ መኖር የሚችል ነው ፡፡ ለሰውም የማይጠቅም ሰብሎቹንም የሚያቀጭጭና የሚያጠፋ ክፉ በሽታ ነው አረም፡፡ መጥፎ ስሜት፣ ብሽሽቅና እልኽኝትም እንዲሁ ነው ። በሰው አዕምሮ ቦታ ከያዘና በህብረተሰቡ ውስጥ ከተሰራጨ የግልና ማህበራዊ ኑሮ የሚያቃውስ ፣ ሀገር ጭምር ሊያፈርስ የሚችል ደዌ ነው ። በሰብል መሀል የበቀለ አረም ከተስፋፋ በኋላ መንቀሉ በራሱ ችግር ነው፡፡ አረሙን ለመንቀል በሚደረገው ጥረት ሰብሎች ይጎዳሉ፡፡ አረሙም ብቅ ጥልቅ የማለት ባህሪ ስለሚኖረው ዝናብ በመጣ ቁጥር መልሶ የሚስፋፋ ነው፡፡ በክፋት ስሜትና መጥፎ አስተሳሰብ የጥላቻ ብሽሽቅና የጥፋት ፖለቲካ የሚያራምዱ ሰዎችም ልክ እንደ አረሙ ናቸው ፡፡ አስተሳሰቡና አመለካከቱም አዕምሮ ውስጥ ተደብቆ ስለሚቀመጥ በሆነ ጊዜ ሊያገረሽ የሚችል ነው ። በመሆኑም ሰብል አጥፊ አረሙንም ይሁን አገር አጥፊውን የተሳሳተና መጥፎ አመለካከት ማጥፋት የሚቻለው አስቀድሞ በመከላከል ነው፡፡ በዘመኑ ቴክኖሎጂ አረምን በራሳቸው የሚከላከሉ ሰብሎች በምርምር እየተገኙ ነው፡፡ ሰውም ራሱ በራሱ ለራሱና ለሀገር አደገኛ የሆኑ መጥፎ አመለካከቶችን ራሱ በራሱ መከላከል መቻል አለበት፡፡ ታላቁ ፈላስፋ አርስቶትል እንዳለው በህይወት መንገድ የሰው ልጆች ጉድኝት ፣ንግግር፣ክርክር እና ውይይቶች በስህተት( Fallacy) የተሞሉ ናቸው ፡፡ ይህንን በመረዳት የሰው ልጅ ተጠያቂያዊ አስተሳሰብን በማጎልበት ወደ እውነት ለመምጣት ሁሌም መጣር እንዳለበት መክሯል ፡፡ በአለማችን ላይ ማህበራዊ ሚዲያዎች በመስፋፋታቸው የሰው ልጅ የሚዲያ እና ፖለተካ ተሳትፎ ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ህብረተሰቡ ልቅ በሆነ መንገድ የሚሰራጩ መረጃዎችን በአግባቡ ለመጠቀም የ Fallacyን ምንነት ጠንቅቆ ማወቅ አለበት፡፡ በእርግጥ በሰለጠኑ ሀገራት ይሄ ችግር እምብዛም አይታይም፡፡ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ያላደጉ ሀገራት የመረጃ አጠቃቀም ዕውቀት ማነስ ትልቅ ችግር እያስከተለ ነው፡፡ Fallacy ምንድነው? ቀጥታ ትርጉሙ በመረጃ ውስጥ የሚቀርብ የሀሳብ ጉድለት ወይም ያለመሟላት ነው፡፡ ይህም ማለት በሚሰራጩ መረጃዎች ውስጥ የሚቀርቡ የመከራከርያና የንግግር ሀሳቦች ያለመሟላታቸው፣ ተስተካክለው ያለመገኘታቸው፣ ስህተት መኖሩን፣ እውነታው አሳማኝ ወይም አጥጋቢ ያለመሆን ወይም የመደበላለቅና የመምታታት ሁኔታ መኖር ነው፡፡ Fallacy በማወቅ ወይም ባለማወቅ በሚያጋጥም የመረጃ ስርጭት፣የክርክር ሀሳብ ወይም የሀሳብ ፍሰት በሚታይ ስህተት የሚገለጽ ነው፡፡ አንድ ሰው ለራሱ ጥቅምና ፍላጎት እያወቀና ሆን ብሎ በተለያዩ ስልቶች Fallacy እንዲኖር ሊያደርግ ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡- መረጃንና ሀሳብን በትክክለኛ መንገድ ያቀረቡ በማስመሰል መረጃን አጠማዞ ሌላውን ግራ ማጋባት(የቃላት ጫወታ በመጠቀም) ሀሰትንና እዉነትን ቀላቅሎ በማቅረብ ማምታታት ስሜታዊ የሆኑ ቃላቶችን በመጠቀም ሌላው ስህተት ውስጥ እንዲገባ ማድረግ…ወዘተ… በሌላ በኩል ባለማወቅ የሚፈጠሩ Fallacy የሚከተሉት ባህሪዎች አሉት፡፡ የመረጃ ወይም የክርክር ይዘት እያወቁ የቋንቋ አጠቃቀም ችግር ሲኖር፡፡ የመረጃን ጭብጥ በአግባቡ ማቀናጀትና ስርአት ማስያዝ ሳይቻል ሲቀር በሚፈጠር ስህተት፡፡ ወዘተ…ናቸው፡፡ በመሆኑም Fallacy በሀሳብ መንደርደርያና መደምደሚያ ላይ በመሸሸግ መጥፎውንና ጥሩውን ቀላቅሎ የሀሰትን መርዝ በእውነተኛ ማር የማላስ አይነት ተግባር ነው፡፡ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት በአሁኑ ወቅት ከማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋትና ከተጠቃሚዎች ቁጥር መብዛት ጋር ተያይዞ Fallacy ያለባቸው ሀሰተኛ መረጃዎች በስፋት እየተንሸራሸሩ ነው፡፡ የእልህና የብሽሽቅ ይዘት ያለባቸው መረጃዎችን ተደራሽ ለማድረግ የሚንሸራሸሩ ጽሁፎች እና ምስሎች በሙሉ በፋላሲ የተሞሉ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀሰተኛ መረጃዎች በማህበራዊ ሚዲያ እንዲንሸራሸሩ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ዋነኛው ተጠቃሚው ስለ Fallacy ያለው ግንዛቤ አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እንደ አረም በመዛመት ከቁጥጥር ውጪ ሊሆኑ ወደ ሚችልበት ደረጃ እየደረሰ ነው፡፡ Fallacy በየትኛው ቦታ አለ፡፡ባደጉትም ባላደጉትም ሀገራት በማህበራዊ ሚዲያዎች ይሰራጫል፡፡ሆኖም ግን ባላደጉት ሀገራት በስፋት የመንሸራሸር እድሉ ከፍተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ባላደጉ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ያሉባቸው የአዕምሮ ንቃተ ህሊና እና ዕውቀት ማነስ ምክንያት ነው፡፡ እንደ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ዋትስ አፕ ቫይበርና የመሳሰሉት የማህበራዊ ሚዲያዎች በመረጃ የዳበረ እና የሰለጠነ ማህበረሰብ በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ እንደሆነ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ ይህም በበለጸጉ ሀገራት ውስጥ በገሀድ እየታየ ነው፡፡ በተለይ አሁን ላይ ያደጉ ሀገራት የዚህን ቴክኖሎጂ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በፖለቲካ አመራር ፣ በቢዝነስ ስራ እና በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች ረጅም ርቀት እየተጓዙ ነው፡፡ ታላላቅ መንግስታት ሳይቀሩ የማህበራዊ ሚዲያን ለፖለቲካ አስተዳደር እንደ መረጃ ምንጭ እየተጠቀሙ ነው፡፡ ከማህበራዊ ሚዲያ የሚያገኙትን መረጃዎች በብቁ ባለሙያዎች በማስተንተንና እውነታውን በማጣራት የተሳሳተውን ጥለው ተአማኒውን በመውሰድ ስኬታማ ስራዎችን እየሰሩበት ነው፡፡ ከዚህም ባለፈ ማህበራዊ ሚዲያ ከሌሎች ሚዲያዎች ይበልጥ ተደራሽ በመሆኑ ህዝቡ ጋር ለመድረስም እንደ አማራጭ እየተጠቀሙ ነው፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ ባደጉት ሀገራት ትልቅ ትሩፋት እያስገኘ ቢሆንም ግን በተቃራኒው ባላደጉት ሀገራት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ አመዝኖ እየታየ ነው፡፡ በእነዚህ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች በአብዛኛው ያልተማሩ እና የአዕምሮ ንቃተ ህሊናቸው በሚገባ ያልዳበረ መሆኑ እንደ ምክንያት ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ በሀገር እና በህዝብ ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የሀሰት መረጃዎችን ማሰራጨት እና በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ መረጃዎችን ሙሉ ለሙሉ ትክክል አድርጎ የማመን እና የመቀበል ችግሮች ባላደጉት ሀገራት በስፋት ይታያሉ፡፡ ያደጉት ሀገራት ከደረሱበት የስልጣኔ ደረጃ ስንዴውን ከእንክርዳድ የመለየት ብቃትና ችሎታ ሲኖራቸው እንደኢትዮጵያ ባሉ ያላደጉ ሀገራት የሚገኙ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ግን ስንዴውን ከነ እንክርዳዱ ሲቆረጥሙ ይታያል፡፡ እነዚህ ሀላፊነት የጎደላቸው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሞች ግጭት በመቀስቀስ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ህይወት እንዲያልፍ ፣ ማህበራዊ ኑሮ እንዲቃወስና የሀገር ሰላም እንዲናጋ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ እንዲሆን ከአንድ አመት በፊት በማይናማር በሮህንጋ ሙስሊሞች ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋ መጥቀስ ይቻላል፡፡ እ.አ.አ ነሀሴ 2017 በተፈጸመው አሳዛኝ ጭፍጨፋ ከ10 ሺህ በላይ የሮሂንጋ ሙስሊሞች አልቀዋል ፡፡ ከ700 ሺሐ በላይ የሚሆኑት ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል፡፡ ይሄ አሳዛኝ ድርጊት የተፈጸመው በፌስቡክ በተደረገ የጥላቻ ቅስቀሳ ነው፡፡ በማይናማር በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ በነበረው ጥላቻ የተነሳ የመብት ጥሰትና ማግለል ለረጅም አመታት የነበረ ቢሆንም አንዳንድ አክራሪ ቡድሂስቶች ህዝቡን ለጥቃት ማነሳሳት የጀመሩት ከቅርብ ግዜ ወዲህ በጀመሩት የፌስ ቡክ ዘመቻ ነው፡፡ በተለይ ታዋቂ የሆኑትና በሮሂንጋዎች ላይ ከፍተኛ ጥላቻ የነበራቸው አሺን ሙራቱ የተሰኙት የቡድሂስት መነኩሴ ከ700 ሺህ በላይ ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ አካውንታቸው ተደጋጋሚ ቅስቀሳዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ይህ ተግባር ያላማራቸው በርካታ ግለሰቦች እርምጃ እንዲወስድ ለፌስቡክ ተቋም ቢያሳዉቁም ፌስቡክ ነገሩን በቸልታ በማለፉ የከፋ ጉዳት ደርሷል፡፡ ግለሰቡ በፌስቡክ ቅስቀሳቸው ሮሂንጋዎች በየእለቱ የቡድሂስት እምነት ተከታዮችን እንደሚገድሉ እና እንደሚደፍሩ የሚያስተላልፉት መልዕክት በህብረተሰቡ ዘንድ እውነት ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ግን ሀሰት ነበር፡፡ ይባስ ብሎ ሁሉም የፌስ ቡክ ተጠቃሚዎች በስፋት ማጋራት መጀመራቸው ከህብረተሰቡ አልፎ በሀገሪቱ ጸጥታ አካላት ድረስ እውነት ተደርጎ ተወሰደ፡፡ በዚህም የተነሳ ከ10ሺ በላይ የሚሆኑ የሮሂንጋ ሙስሊሞች ቤቶቻቸው እየተቃጠሉባቸው እና በተለያየ የጦር መሳሪያዎች ተጨፈጨፉ፡፡ የተረፉት ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዱ፡፡ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ፌስቡክ የሀሰት መረጃ አሰራጭተዋል የተባሉ ግለሰቦችን አገደ፡፡ ቅስቀሳዉም ከእውነት የራቀና በተወሰኑ ግለሰቦች ቅስቀሳ የተፈጠረ መሆኑ ተረጋገጠ፡፡ በሀገሪቱ የፖለቲካ ተንታኝ እና ተመራማሪ የሆኑት David Mathenson sbsnews.com ለተባለ ሚዲያ በሰጡት አስተያየት ከሀገሪቱ ህዝብ አብዛኛው ያልተማረና ሰለማህበራዊ ሚድያዎች ግንዛቤ የሌለው በመሆኑ መረጃውን ሙሉ ለሙሉ እውነት አድርጎ እንደተቀበለው ተናግረዋል፡፡ ባላደጉትና ባልሰለጠኑ ሀገራት የማህበራዊ ሚድያዎች ጠቀሜታቸው ሳይሆን ጉዳታቸው ጎልቶ እየታየ መሆኑን ሁሉም ቢስማማበትም በመፍትሄው ዙሪያ እስካሁን የተሰራ ስራ የለም፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ብዙ ብሄር ብሄረሰቦችና ሀይማኖቶች ተቻችለው በሚኖሩበት ሀገር እየታየ ያለው ሀላፊነት የጎደለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ካላት 100 ሚሊዮን በላይ የህዝብ ቁጥር ከ16 ሚልዮን በላይ የሚሆነው የማህበራዊ ሚድያ ተጠቃሚ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ይሄ ቁጥር ከህዝብ ብዛት አንጻር አነስተኛ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ሆኖም ግን አብዛኛዎቹ ተጠቃሚዎች ሚዲያዉን እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ ችግሮችን በውይይትና በመነጋገር ከመፍታት ይልቅ ሀሰተኛ የጥፋት መረጃዎችን ሲያሰራጩ ይስተዋላሉ፡፡ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን፣ ከመቀራረብ ይልቅ መራራቅን፣ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን፣ ከመደጋገፍ ይልቅ፣መገፋፋትን፣ ከይቅርታ ይልቅ በቀልን በአጠቃላይ ከገንቢ እና እውነተኛ መረጃዎች ይልቅ አፍራሽና ሀሰተኛ መረጃዎችን የማሰራጨት አሳፋሪ እና አንገት የሚያስደፋ ተግባራት በስፋት እያስተዋልን ነው፡፡ ወርቃማ ግዜያቸውን በማባከን ቀኑን ሙሉ የኔ ዘር እንደዚህ የእሱ ዘር እንደዛ በማለት ሲባዝኑ የሚውሉ ሰዎችን የማየት ያህልም የሚሳዝን የለም፡፡ ሀይማኖትን የማንቋሸሽ፣ የግለሰቦችን ስም በመጥራትና ምስላቸውን አቀነባብረው በመለጠፍ ከህሊናቸው ተነጥለው የሚዳክሩ ግለሰቦችም በገሀድ ይታያሉ፡፡ በቅርቡ በቡራዩ በተከሰተው አደጋ ሲሰራጩ የነበሩ የሀሰት መረጃዎች እና ሀሰተኛ ምስሎች የዚሁ ነጸብራቅ ናቸው፡፡ እነዚህ ክፉና የተዛባ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻቸው አንድን አካል በመነጠል ችግሩን እንደፈጠረ አድርገው አብዛኛው የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ አድርገዋል፡፡ የጥፋቱ መነሻ በፖሊስ ምርመራ ሳይጣራ በቡድኖችና በግለሰቦች ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከማፋፋም ጀምሮ በተለያዩ የአለም አካባቢዎች የተፈጸሙ አሰቃቂ ግድያዎችን ሆን ብለው በማቀነባበር በህብረተሰቡ ውስጥ ረጭተዋል፡፡ ይህ ተግባር እነሱንም ፣ህዝቡንም ሀገሪቱንም የሚጎዳ ተግባር መሆኑን እያወቁ በመጥፎ ስሜት ያደረጉት ቢሆንም አብዛኛው ህብረተሰብ ግን መረጃዉን እውነት አድርጎ መቀበሉና ማሰራጨቱ አሳዛኝ ነው፡፡ አሁንም በምን ደረጃ ላይ ነን የሚያስብል ነው፡፡ በማህበራዊ ሚድያዎች የሚሰራጩ መረጃዎች በስህተት የተሞሉ መሆናቸውን በመገንዘብ የመረጃውን ምንጭ እና ትክክለኛነት መረዳት የግድ ይላል፡፡ይህን ለማድረግ የግድ በቀለም ትምህርት መግፋት ላያስፈልገን ይችላል፡፡ አዕምሮን ማሰልጠን በቂ ነው፡፡ ታላቁ የፊዚክስ ሊቅ አልበርት አንስታይንም እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ ``Learning is experience, everything else is information`` ቸር እንሰንብት