የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኮፐንሀገን ከተማ በድጋሚ በረራ ሊጀምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ኮፐንሀገን ከተማ በድጋሚ በረራ ሊጀምር ነው
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 17/2015 የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዴንማርክ ኮፐንሀገን ከተማ ከግንቦት 14/2015 ጀምሮ በድጋሚ በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ።
አየር መንገዱ በሳምንት አምስት ጊዜ ወደ ከተማዋ የመንገደኞች በረራ እንደሚያደርግ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ ገልጿል።
የበረራው መጀመር አየር መንገዱ በሰሜን አውሮፓ እና በምዕራባዊ ስካንዲኒቪያ ያለውን ተደራሽነት ለማስፋት የጎላ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል።
በረራው በአውሮፓና አፍሪካ መሐል ያለውን የአየር ትስስር በማጠናከር ሁለቱ አህጉራት በዲፕሎማሲ፣ በንግድ እና ቱሪዝም ያላቸውን ትብብር የሚያሳልጥ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ እ.አ.አ ሕዳር 1999 ወደ ኮፐንሀገን በረራ ጀምሮ ከአራት ዓመት በኋላ አገልግሎቱ ተቋርጦ እንደነበር በመረጃው አስታውሷል።