በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 16/2015 በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በመሳተፍ ለአገራቸው ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት በላቀ ሥራ አፈጻጸም የሁለተኛ ደረጃ የልህቀት ዋንጫ ተሸላሚውን ሆራይዞን አዲስ ጎማ ፋብሪካን ዛሬ ጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ የጥራት ድርጅት የበላይ ጠባቂ የሆኑት ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በጉብኝታቸው የፋብሪካውን የሥራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን የሥራ ክንውኑን አድንቀዋል።
በውጭ ይኖሩ የነበሩት ሼህ ሙሃመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ለኢትዮጵያ ባላቸው ተቆርቋሪነት ሜድሮክ ኩባንያን በማቋቋም ትልቅ ኢንቨስትመንት ማድረጋቸውን አስታውሰው፤ አድንቀዋቸዋል።
ከትንሽ ጀምሮ ትልቅ ደረጃ መድረስን በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ ያሉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ኢንቨስትመንት መስኮች ላይ መሰማራት እንደሚገባቸው ምሳሌ ይሆናሉ ብለዋል።
ይህንንም ተከትሎ የዳያስፖራ አባላት በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በመሳተፍ ለአገራቸው ምጣኔ ኃብታዊ እድገት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ነው ጥሪያቸውን ያቀረቡት።
ከሜድሮክ እህት ኩባንያዎች አንዱ የሆነውና ብቸኛው የጎማ አምራች ፋብሪካ ሆራይዞን አዲስ ጎማም በሥራ ዕድል ፈጠራና በሰራተኞች አያያዝና የሥራ ባህል ተምሳሌታዊ ጎኖች እንዳሉት ገልጸዋል።
በሰራተኞች እንክብካቤ፣ ቤተሰባዊ አሰራር፣ የድርጅት አመራር ጥበብና በጥራት ደረጃዎች የጠበቀ አመራረት ረገድ ለሌሎች ድርጅቶች አርአያ የሆነ ተቋም ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የጎማ ፋብሪካው ምርቶች ለአገር ህልውናና ለኢኮኖሚዊ ዕድገት የሚበጁ በመሆናቸው በቀጣይነት የጥራትና ተወዳዳሪነት ደረጃውን ማስቀጠል እንደለበት ጠቁመዋል።
ከፋብሪካው ምርቶች መካከል ባለሦስት እግር ተሽከርካሪ፣ የቤት መኪና፣ ቀላልና ከባድ ጭነት ተሽከርካሪ፣ የግሬደር፣ የትራክተር ጎማዎችንና የመከላከያ ሠራዊት የሚያገለግሉ ተሽከርካሪ ጎማዎች ይገኙበታል።