የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ107 ሚሊዮን ዶላር የብድር ሥምምነት ረቂቅ አዋጅን ለቋሚ ኮሚቴ መራ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ107 ሚሊዮን ዶላር የብድር ሥምምነት ረቂቅ አዋጅን ለቋሚ ኮሚቴ መራ
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 16/2015 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውለውን ከ107 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የብድር ሥምምነት ረቂቅ አዋጅ በመደገፍ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መራ።
የኢፌዴሪ 6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 9ኛ መደበኛ ስብስባውን አካሂዷል።
ምክር ቤቱ የ2ኛ ዓመት የሥራ ዘመንን 8ኛ መደበኛ ጉባኤ ስብሰባ ቃለ ጉባኤን በመመርመር በሙሉ ድምጽ በማጽደቅ መደበኛ ስብሰባው ጀምሯል።
በመቀጠልም የኢትዮጵያ መንግሥት ከቱርክና ከተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች መንግሥታት ጋር በአሳልፎ መስጠትና የወንጀል ጉዳዮች የጋራ የሕግ ሥምምነት ረቂቅ አዋጆችን በመመርመር ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
የኤክሳይዝ ታክስ አዋጅን፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሠራተኞች ደንብና የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሠራተኞች አስተዳደር ደንብን ለማሻሻል የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለዝርዝር እይታ መምራት ምክር ቤቱ የወሰናቸው ውሳኔዎች ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር የደረሰውን የብድር ሥምምነት ረቂቅ አዋጅ በመመርመር ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።
ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር የተገኘው ገንዘብም በሁለተኛው ምዕራፍ ዘላቂ የመሬት አያያዝን ለማረጋገጥ የሚደረገውን የልማት ሥራ በመደገፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው በማብራሪያው ቀርቧል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር የደረሰው ከ107 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የሚሆነው የብድር ሥምምነትም ከወለድ ነፃና በረጅም ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተጠቁሟል።
የፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የብድር ሥምምነቱም ዘላቂ የመሬት አያያዝን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በመገንዘብ ለዝርዝር እይታ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ መርቷል።
የምክር ቤቱ አባላትም በኢትዮጵያ በመሬት አያያዝ ችግር የመሬት መራቆት፣ ዝናብ መቆራረጥ፣ የአፈር ለምነት መቀነስ፣ የገጽና የከርሰ ምድር ውሃ መቀነስ እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ከዓለም አቀፉ የልማት ማኅበር የተገኘው የገንዘብ ብድርም መንግሥት እየተባባሰ የመጣው የመሬት አያያዝ ችግር ምላሽ ለመስጠት የሚያደርገውን ጥረት እንደሚደገፍ ተናግረዋል።
ገንዘቡ ወደ ተግባር ሲገባም በኢትዮጵያ የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በመደገፍ ለወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠርም ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አንስተዋል።
ገንዘቡን በሚገባ ተግባር ላይ እንዲውልም የተሻለ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በማከናወን ወጣቱንና የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በማቆራኘት ዘላቂ የመሬት አያያዝን ማሳደግ እንደሚያስፈልግም የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል።
ምክር ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ ለመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሰጡትን ሹመት በ10 ተቃውሞ፣ በ2 ተዓቅቦና በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።
በወቅቱም የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትርና የግብርና ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አለሙ ስሜ (ዶ/ር) እና ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) መንግሥትና ሕዝብ የጣለባቸውን የሥራ ኃላፊነት በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ-መሃላ ፈጽመዋል።