ቀጥታ፡

በአማራ ክልል 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበላቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እየተከናወነ ነው

ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 16/2015 በአማራ ክልል በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበላቸው 250 የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡

በምዕራብና በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አዋሳኝ ወረዳዎች ለሚገነባው የአንገረብ ወንዝ ግድብ ግንባታና የመስኖ ልማት ፕሮጀክት የጥናትና ዲዛይን ሥራ ማስጀመሪያ ትውውቅ መድረክ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።

የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ዳኝነት ፈንታ እንደተናገሩት፣ በበጀት ዓመቱ በክልሉ የተለያዩ ዞኖች የተጀመሩት አነስተኛና መካከለኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ 30ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አላቸው።

ግንባታቸው ከተጀመሩት የመስኖ ፕሮጀክቶች መካከል 15 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው 127 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ዘንድሮ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ ግብ ተጥሎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ 45 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው 300 የመስኖ ፕሮጀክቶች የጥናትና ዲዛይን ሥራቸው እየተከናወነ ሲሆን፣ "በቀጣይ የዲዛይን ሥራው ሲጠናቀቅ ወደ ግንባታ ሥራ ይገባል" ብለዋል።

በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር አማካኝነት በክልሉ ግንባታቸው የተጀመሩና 22 ሺህ 310 ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያላቸው አራት ነባር ከፍተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአሁኑ ወቅት በጥሩ የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚገኙም ዶክተር ዳኝነት አመልክተዋል።

ምናልባት የ5 ሰዎች፤ የቆሙ ሰዎች እና ከቤት ውጪ ምስል

በመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር የመስኖ ፕሮጀክቶች ዝግጅት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ሳሙኤል ሁሴን በበኩላቸው፣ በከፍተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋለውን የግንባታ መጓተት ለማስቀረት በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የተቋራጮች አቅም ማነስ እንዲሁም ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ የጥናትና ዲዛይን ሥራዎች አለመስራት ለመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተት ተጠቃሽ ምክንያት መሆናቸውን መሪ ስራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።

እነዚህ ችግሮች እንዲፈቱ የማረምና የማስተካካል ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

"በምዕራብና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች አዋሳኝ ወረዳዎች የሚገነባው የአንገረብ ወንዝ ግድብና የመስኖ ልማት ፕሮጀክት 50ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም አለው" ያሉት ደግሞ የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሱራፌል ገብረጊዮርጊስ ናቸው።

ለፕሮጀክቱ ግብአት እንዲሆን የመጀመሪያ ደረጃ የመስክ ቅኝት መካሄዱን ጠቁመው፣ በቀጣይ ሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ የጥናትና ዲዛይን ሥራውን በማጠናቀቅ የግድቡ ግንባታ ሥራ ለመጀመር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚያሰራው የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር መሆኑን ጠቁመው፣ የጥናትና ዲዛይን ሥራውን የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይንና ሱፐርቪዥን ሥራዎች ኮርፖሬሽን መሆኑን አስታውቀዋል።

በፕሮጀክት ማስተዋወቅ መድረክ ላይ የፌዴራል፣ የክልልና የሁለቱ ዞኖች የመስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት የሥራ ሃላፊዎችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አጋር አካላት ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም