ቀጥታ፡

የፋብሪካው ሠራተኞችና አስተዳደር ለተፈናቃዮች ከ788 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

ነቀምቴ መስከረም 24/2011 የአርጆ ዲዴሣ ስኳር ፋብሪካ ሠራተኞችና  አስተዳደር  ሰሞኑን  ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ788 ሺህ ብር በላይ ድጋፍ  አደረጉ ። የፋብሪካው ሠራተኞች ድጋፍ ያደረጉት በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች  በተፈጠረው ግጭት ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ  ወገኖች ነው፡፡ የፋብሪካው ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምትኩ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት የፋብሪካው ሠራተኞች መስከረም 22  ቀን 2011 ባደረጉት  ስብሰባ 551 ሺህ 325 ብር በአንድ ጊዜ ክፍያ ከወርሃዊ ደመወዛቸው እንዲሰጥ ወስነዋል ። ከእዚህ በተጨማሪ 137 ሺህ 500 ብር ግምት ያለው ከ62 ኩንታል በላይ ስኳር ለተፈናቃዮች መሰጠቱን የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ የፋብሪካው አስተዳደርም 100 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጉን አመልክተዋል፡፡ ከፋብሪካው ሠራተኞች መካከል አቶ ኪሲ ጨመዳ በሰጡት አስተያየት ለወገን ደራሽ ወገን  በመሆኑ በወር ከሚያገኙት ደመወዛቸው 10 በመቶ ተቀንሶ ለተፈናቃዮች እንዲሰጥ መወሰናቸውን ተናግረዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም የፋብሪካው ሠራተኞች አረጋግጠዋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም