ቀጥታ፡

በጣና ሐይቅ ላይ የሚካሔደውን የታንኳ ቀዘፋ የቱሪስት መስህብ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ ነው--የባህርዳር ከተማ አስተዳደር

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ጥር 16/2015 በጣና ሐይቅ ላይ የሚካሄደውን የታንኳ ቀዘፋና የጀልባ ትርኢት የባህር ዳር ከተማ ቱሪስት መስህብ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የከተማዋ አስተዳደሩ የባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።

ጥርን በባህር ዳር አካል የሆነው ስድስተኛው የጣና ሐይቅ የታንኳ ቀዘፋና የጀልባ ትርኢት መርሐግብር ዛሬ ተጀምሯል።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ጋሻው እንዳለው ከተማዋ በተፈጥሮ ያላትን የመስህብ ሃብት በመጠበቅና በማልማት የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።

በየዓመቱ በጥር ወር እየተካሄደ የሚገኘው የጣና ሐይቅ የታንኳ ቀዘፋና የጀልባ ትርኢት የዚሁ እቅድ አንዱ አካል መሆኑን አመልክተዋል።

May be an image of 1 person, standing and outdoors

ዛሬ በተጀመረው ትርኢት 70 ጀልባዎችና 60 ታንኳዎች እንደሚሳተፉ ጠቅሰው፤ ይህም የከተማ አስተዳደሩ የቱሪስት መዳረሻዎችንና የጎብኚዎችን ቁጥር እንዲጨምር እድል እንደሚፈጥርለት ገልጸዋል።

ትርኢቱ የቱሪዝም ዘርፉ እንዲጎለብትና እንዲነቃቃ እንዲሁም ሕብረተሰቡ ውሃ ላይ መዝናናትን ባህል አድርጎ እንዲወስድ የበኩሉን ሚና እንደሚጫወት ነው አቶ ጋሻው የገለጹት።

የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እና እንግዶች በቀድሞው ጊዮን ሆቴል ዳርቻ መካሄድ በጀመረው የታንኳ ቀዘፋ እና የጀልባ ትርኢት በመከታተል ላይ ናቸው።

የጣና ሐይቅ የታንኳ ቀዘፋና የጀልባ ትርኢት ከስድስት ዓመት በፊት በ30 ታንኳና በ40 ጀልባዎች መጀመሩን ከባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም