በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ቅድመ መከላከል ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ቅድመ መከላከል ላይ በትኩረት ሊሰራ ይገባል
አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 16/2015 በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ኅብረት ገለጸ።
ኅብረቱ ሁሉን አቀፍ የጤና ተደራሽነትና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ያሉበትን ደረጃና በዘርፉ ያለውን የፋይናስ አቅርቦት የሚዳስስ ጥናት ላይ ውይይት አካሂዷል።
ጥናቱን ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ኅብረት ከማቴዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ እንዲሁም ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መሆኑን ተጠቅሷል።
ተላላፊ ያልሆኑ ሕመሞች ኅብረት ዋና አስተባባሪ አቶ ወንዱ በቀለ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የልብና የደም ሥር፣ የካንሰር፣ የልብ፣ የስኳር፣ የመተንፈሻ አካልና መሰል ህመሞች በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ሥጋት ሆኗል።
በኢትዮጵያ ችግሩ በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸው ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እየተሰጠ የሚገኘው የጤና አገልግሎት ከ50 በመቶ በታች መሆኑን ገልጸዋል።
ያም ብቻ ሳይሆን መንግሥት ካለፉት 10 አመታት ወዲህ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚመድበው በጀት ከአጠቃላይ የጤና በጀት 32 በመቶ መሆኑን ተናግረዋል።
በአንጻሩ፤ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ለህክምና የሚያስፈለገው ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ ዜጎች በጤና እጦት ለችግር እየተጋለጡና ይህም ለድኅነት ተጋላጭ እየዳረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከልና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚሰጠው የጤና አገልግሎት ሽፋኑ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኅብረተሰቡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተካከል፣ ከአልኮል መጠጥና ሲጋራ መቆጠብ የአካል ብቅት እንቅስቃሴን ባህል ማሳድግ ያስፈልጋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ የጤና መድኅን አገልግሎት የፕሮግራም ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉቀን አርጋው በበኩላቸው መንግሥት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የጤና ሥጋት የሆነውን ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የህክምና አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል።
በተለይም በጤና መድኅን ፕሮግራም 45 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለ ሲሆን በቀጣይ ዓመት ከ50 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የታቀደ መሆኑን ገልጸዋል።
በውይይቱም ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎቹ ህክምና ተደራሽነትና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተግባራዊ በማድረግ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ አጋር አካላት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።