ለዳያስፖራ አደረጃጀቶች የእውቅና የምስጋና መርኃ ግብር በመጪው ሐሙስ ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለዳያስፖራ አደረጃጀቶች የእውቅና የምስጋና መርኃ ግብር በመጪው ሐሙስ ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ ጥር 16/2015 (ኢዜአ) ለዳያስፖራ አደረጃጀቶች የእውቅና የምስጋና መርኃ ግብር በመጪው ሐሙስ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ገለጹ።
በመርኃ-ግብሩ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ 52 የዳያስፖራ አደረጃጀቶች እውቅና ይሰጣቸዋል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ እውቅናው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።
የእውቅና መርኃ-ግብር የተዘጋጀው ዳያስፖራው በተደራጀ መልኩ ያከናወናቸውን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ፣ የገጽታ ግንባታና የኃብት ማሰባሰብ ተግባራትን እንዲሁም ያስገኛቸው ውጤቶችን ለማበረታታትና ምስጋናን ለማቅረብ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ የተሻለ አደረጃጀትና አፈጻጸም ያላቸውን በውጭ አገራት ለሚገኙ 51 አደረጃጀቶችና አንድ በአገር ውስጥ ለሚገኝ ጥላ ማኅበር እውቅና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
አደረጃጀቶቹ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቅ፣ በኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ያካበቱትን እውቀት፣ ክህሎትና ኃብት በመጠቀም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በመጪው ሐሙስ ጥር 18 ቀን 2015 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ በሚደረግ መርኃ-ግብር እውቅና እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
ከእውቅና መርኃ-ግብሩ ባሻገር የዳያስፖራ አደረጃጀቶቹንና ያከናወኗቸው ተግባራትን የሚያስተዋውቅ መጽሐፍ ምረቃ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ከእውቅና መርኃ-ግብሩ ማግስት የዳያስፖራው ተወካዮችና የአደረጃጀት ኃላፊዎች ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማስጎብኘት ዕቅድ ተይዟል ብለዋል።
የእውቅና መድረኩ በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ ሌሎች ዘርፎችን በማካተት የሚካሄድ መሆኑንም አስረድተዋል።
በእውቅና መርኃ-ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች፣ የተቋማት አመራሮች፣ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።