የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ላልተገባ ወጪ እየዳረገን ነው...የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ላልተገባ ወጪ እየዳረገን ነው...የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች
ሆሳዕና መስከረም 24/2011 በተደጋጋሚ የሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ላልተገባ ወጪ እንደዳረጋቸው የሆሳዕና ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡ በከተማዋ ሔጦ ቀበሌ የሚኖሩት ወይዘሮ እቴቱ ለማ በአካባቢያቸው መብራት በየጊዜው እንደሚጠፋና ለቀናትም ሳይመጣ እንደሚቆይ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡ ድንገት በሚከሰት የኃይል መቆራረጥ ደረቅ እንጀራን ጨምሮ በመብራት አገልግሎት የሚዘጋጁ የእለት ምግቦችና ሌሎች ዕቃዎች ላይ ጭማሪ በመደረጉ ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መንግስት ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ሊሰጠን ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ እስከ አሥር ቀን ድረስ ላይመጣ እንደሚችል የገለጹት ደግሞ በከተማው የማረሚያ አካባቢ ነዋሪ አቶ ልኡልሰገድ ማሞ ናቸው፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ ማታ ማታ ጨለማው የጸጥታ ስጋት እያሳደረባቸው በመሆኑ በመንግስት በኩል ፈጣን ምላሸ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ በኃይል መቋረጥ ምክንያት በቤት ውስጥ ምግብ ለማብሰል ከመቸገራቸው በተጨማሪ ልጆቻቸው ማታ ማታ ትምህርታቸውን ለማጥናት መቸገራቸውንና በእዚህም ለሻማና ለሌሎች ወጪዎች እየተዳረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል ፡፡ በሆሳዕና ከተማ ቤተል ቀበሌ የሚኖረው ወጣት ግርማ በለጠ በበኩሉ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በሚተዳደርበት የህትመት ሥራው ላይ እንቅፋት እየፈጠረበት መሆኑን ተናግሯል፡፡ ኃይል በተደጋጋሚ በመጥፋቱ ለጄኔሬተር ወጪ ከመዳረጉ በተጨማሪ ቤተሰቡን በአግባቡ ሰርቶ ለማስተዳደር ችግር እየገጠመው መሆኑን አስረድቷል፡፡ በደቡብ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሆሳዕና ዲስትሪክት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ገብሬ ማሴቦ ለችግሩ መከሰት ዋናው ምክንያት የግቤ ኤሌትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ምሶሶዎች በእርጅናና በተለያየ ምክንያት ለጉዳት መዳረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል። ችግሩን በዘለቄታ ለመፍታት ከግቤ እስከ ሆሳዕና ያሉ ያረጁ የእንጨት ምሶሶዎችን ወደ ብረት ምሰሶ የመለወጥ ሥራ በአሁኑ ወቅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የስርጭት መስመሩን ወደ ብረት የመለወጥ ሥራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ችግሩ መፍትሄ እንደሚያገኝ አመልክተዋል። ማረሚያ እየተባለ በሚጠራው የከተማው አካባቢ ለተፈጠረው የኃይል አገልግሎት ችግር ምክንያቱ የትራንስፎርመር ማርጀት መሆኑን አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ከክልሉ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምትክ ትራንስፈርመር በመምጣቱ በፍጥነት ምላሽ እንደሚያገኝ ገልጸዋል፡፡