ክለቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበትን የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብሮችን ማስፋት አለባቸው

107

አዲስ አበባ (ኢዜአ)ጥር 16/2015 ክለቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበትን የገቢ ማሰባሰቢያ መርኃ ግብሮችን ማስፋት እንዳለባቸው የዘርፉ ባለሙያ ዶክተር ጋሻው አብዛ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የኢትዮጵያን እግር ኳስ አጠቃላይ ነባራዊ እውነታዎችና የውድድር ሂደቱን በማስመልከት በተደረገው ጥናት ላይ ውይይት መደረጉ ይታወቃል።

በአሜሪካ ሜሪላንድ ታውሰን ዩንቨርሲቲ የስፖርት አስተዳደርና የቢዝነስ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ጋሻው አብዛ፤ የጥናት ውጤቱን በማቅረብ የዘርፉን መልካም እድሎችና ተግዳሮቶች በዝርዝር አስረድተዋል።

በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ዶክተር ጋሻው የስፖርት ዘርፍ በተገቢው መንገድ ከተመራ ከፍተኛ ገቢ በማመንጨት ለአገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ ሚና ያለው መሆኑን ይናገራሉ።

የስፖርት ዘርፍ ከስፖርተኞችም ሆነ ከስፖርት ግብዓት አቅራቢዎች ለበርካቶች ቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሥራ እድል የሚፈጠርበት መሆኑንም ነው የገለጹት።

አንዳንድ አገራት ከስፖርት የሚያገኙት ገቢ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው ለአብነትም የሰሜን አሜሪካ እግር ኳስ በዓመት 10 ቢሊዮን ዶላር ከቴሌቪዥን መብት ሽያጭ ብቻ ገቢ እንዳለው ገልጸዋል።

በአፍሪካ ደረጃም የደቡብ አፍሪካ የራግቢ ስፖርት እንደ ጥሩ ተሞክሮ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት አሁናዊ ሁኔታ ግን አብዛኞቹ ስፖርተኞች ደሞዝን ጨምሮ የገቢ ምንጫቸው ከመንግሥት በጀት ላይ የተንጠለጠለ ስለመሆኑ ነው ያነሱት።

ይህም አዋጭ አለመሆኑንና መንግሥት ስፖርቱ ራሱን በራሱ የሚደግፍበት ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች ላይ ማተኮር አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ስፖርት ዋናው ችግር የስፖርት አስተዳደር ችግር ነው ያሉት ዶክተር ጋሻው ብቁ አመራርና ባለሙያ ማፍራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

እንዲሁም በስፖርት ፖሊሲው መሰረት ክለቦችና የስፖርት ማኅበራት የራሳቸውን ገቢ አመንጭተው፤ ራሳቸውን መደገፍ አለባቸው ነው ያሉት።

ይህንንም ተከትሎ ክለቦች በድጋፍ ሥምምነት፣ ከቴሌቪዥን መብት ሽያጭ፣ ከማልያና አልባሳት ሽያጭና መሰል የገቢ ምንጫቸውን አጎልብተው ራሳቸውን መቻል እንደሚችሉ ነው ያብራሩት።

ከዚህ በተጨማሪ የተሻለ ገቢ ለመፍጠርና ለቁጥጥር ሥርዓት ምቹ እንዲሆን ክለቦችን ሕዝባዊ ማድረግም ሌላኛው ወሳኝ ተግባር መሆኑንም አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም