የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል--ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል--ጤና ሚኒስቴር
ጋምቤላ (ኢዜአ) ጥር 16/2015 የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።
የጊኒ ዎርም በሽታን ለማጥፋት በ2022 የተከናወኑ ስራዎችን የሚገመግመው 27ኛው ዓመታዊ መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተጀምሯል።
በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ደጉማ የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት በቅንጅትና በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የጊኒ ዎርም በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት እየተደረገ ባለው ጥረት በዘርፉ የሚሰሩ የመንግስት ተቋማትና አጋር ድርጅቶች በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ጨምረው ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት የበሽታውን ስርጭት ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በተከናወኑ ስራዎች የበሽታውን ስርጭት መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የበሽታው ስርጭት በጋምቤላ ክልል አቦቦና ጎግ ወረዳዎች የሚታይ ቢሆንም በእነዚህ ወረዳዎች የስርጭት መጠኑ መቀነሱን ነው የገለጹት።
ለዚህም ማሳያው በተጠናቀቀው የፈረንጆች ዓመት በወረዳዎች የበሽታው ምልክት የታየው በአንድ ሰውና በሶስት እንሳሳት ላይ ብቻ መሆኑ በመግለጽ።
በመሆኑም በሽታውን ከሁለቱ ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ በማጥፋት ክልሉን ብሎም ሀገሪቱን ከጊኒ ዎርም በሽታ ነፃ ለማድረግ በዘርፉ የሚሰሩ የመንግስትና የአጋር ድርጅቶች ትብብራቸውና ቅንጅታዊ አሰራሮቻቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በተለይም የንፁህ ውሃ አቅርቦትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ ከተቻለ በሽታውን በቀላሉ ማጥፋት ሰለሚቻል በእዚህ ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ሚኒስትር ዴታው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው ባለፉት 30 ዓመታት በሽታውን ለማጥፋት በተደረገው ጥረት የስርጭት መጠኑን ወደ አንድ ከመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን አሰታውቀዋል።
በቀጣይም ኢንስትቲዩቱ ከአጋር አካላት ጋር በመሆን የጥናት፣ የምርምርና የቅኝት ስራዎችን በማጠናከር በሽታውን ከጋምቤላ ብሎም ከኢትዮጵያ ለማጥፋት በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ተንኩዋይ ጆክ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በተከናወኑት ስራዎች የበሽታውን ስርጭት መጠን መግታት ቢቻልም ሙሉ ለሙሉ ማጥፋት አልተቻለም ብለዋል።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት በግብርና ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶች ለሰራተኞቻቸው በቂ የንጹህ መጠጥ ውሃ ያለማቅረብ ችግር አንዱ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በንፁህ መጠጥ ውሃ በኩል የሚታየውን ችግር ለመፍታት ክልሉ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ዓመታዊ የእቅድ አፈፃፀም ግምገማ ላይ የፌዴራል፣ የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።