ቀጥታ፡

ፖሊስ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የአስተዳደር ሕንጻ ላይ የደረሰውን የእሳት አደጋ መንስኤ ላይ ምርመራ እያካሄደ ነው - የከንቲባ ጽህፈት ቤት

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 16/2015 ፖሊስ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የአስተዳደር ሕንጻ ላይ የደረሰውን የእሳት አደጋ መንስኤ ላይ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በአደጋው በሕዝብ መረጃዎች እና ዳታ ላይ የደረሰ አደጋ አለመኖሩን ገልጿል።

የእሳት አደጋው የደረሰው በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በሚገኘው የክፍለ ከተማው የአስተዳደር ሕንጻ ላይ መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመንና ሌብነትን ለመከላከል የዲጂታይዜሽን ስርዓትን ለመተግበር በርካታ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መረጃ ገልጿል።

በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የነበረውን ብልሹ አሰራርና ሌብነትን ለማስተካከልና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ይረዳ ዘንድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስተባባሪነት የዘመናዊ የቢሮ ግንባታና የተቋማዊ ሪፎርምና የዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተገበረ እንደሚገኝ አመልክቷል።

May be an image of tree and outdoors

የኢትዮ ቴሌኮም፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት(አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ)፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ተቋማት የተሳተፉበት የዲጂታል አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ስራ የፊታችን ቅዳሜ ለምረቃ የሚያበቃ ስራ ተከናውኖ እንደነበር አስታውሷል።

ይሁንና ትናንት ምሽት 4 ሰአት ከ48 ደቂቃ ላይ ከፍተኛ ቴክኖሎጂና ግብዓት የፈሰሰበት የክፍለ ከተማው አስተዳደር ሕንጻ የእሳት አደጋ ደርሶበት መሰረተ ልማቱ መውደሙን ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።

በአደጋው የሕዝብ ፋይል፣ ዳታ እና መረጃዎች ላይ የደረሰ አደጋ አለመኖሩን አመልክቷል።የአደጋው ምክንያት በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደበት እንደሚገኝና ምርመራው እንዳለቀ ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግም ጠቁሟል።

የአካባቢው ማህበረሰብ መንግስት የጀመረውን ጥረት ለመደገፍ ከአደጋው ጋር ተያይዞ ማንኛውንም መረጃዎች በመስጠት የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ጽህፈት ቤቱ ጥሪ አቅርቧል።

“አሁንም የጀመርነውን የሕዝባችንን ጥያቄ የመመለስና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የመፍታት ጥረታችንን ማንም ምድራዊ ኃይል ሊያስቆመው አይችልም” ሲልም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም