ኢትዮጵያ ከዴንማርክ ጋር ያላትን የትብብር መስኮች ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት አላት-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን

31

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 16/2015 ኢትዮጵያ ከዴንማርክ ጋር ያላትን የትብብር መስኮች ግንኙነት ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ።

ዴንማርክ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የልማት ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገለጻለች።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የዴንማርክ የልማት ትብብር እና ዓለም አቀፍ አየር ንብረት ሚኒስትር ዳን ጃርገንስን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በውይይቱም አቶ ደመቀ ዴንማርክ የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት አጋር መሆኗን አስታውሰው ሁለቱ ሃገራት በተለያዩ የትብብር መስኮች ግንኙታቸው እንዲጠናከር የኢትዮጵያ ፍላጎት መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ በነበረችበት ወቅት የዴንማርክ መንግስት ለነበረው ሚዛናዊ አቋም ምስጋና አቅርበዋል።

አቶ ደመቀ በሰላም ስምምምነቱ አተገባበር ዙሪያ ለሚኒስትሩ ገለፃ ያደረጉ ሲሆን መንግስት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ግጭት በነበረባቸው አካባቢዎች መሰረታዊ አገልግሎቶች ዳግም መጀመራቸውን እና የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነት እንዲስፋፋ መደረጉን ገልጸዋል።

በግጭት ወቅት የተፈፀሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሽግግር ፍትህ ተጠያቂ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

በጦርነት ተጎጂ የነበሩ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት እና ለማቋቋም መንግስት እቅድ አውጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልጸው ይህንን ጥረት ዴንማርክ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች እንዲደግፉም አቶ ደመቀ ጠይቀዋል።

የዴንማርክ የልማት ትብብር እና አለም አቀፍ አየር ንብረት ሚኒስትር ዳን ጀርገንስ የዴንማርክ እና የኢትዮጵያ የልማት ትብብር አመታትን ማስቆጠሩን አስታውሰው አገራቸው ይህን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የማድረስ ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል።

በመንግሰት እና በህወሐት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙ በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እንደሚረዳ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል።

ሚኒስትሩ ዴንማርክ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የልማት ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም