የከፍተኛ ትምህርት ዲጂታል የትምህርት መረጃ ስርዓት ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 16/2015 የከፍተኛ ትምህርት ዲጂታል የትምህርት መረጃ ስርዓት ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር መገባቱን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የዲጂታል የትምህርት መረጃ ስርዓቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመረጃ አሰባሰብና አስተዳደርን ለማዘመን የሚረዳ መሆኑም ተጠቁሟል።

ትምህርት ሚኒስቴር በዲጂታል የትምህርት መረጃ ስርዓት አጠቃቀም ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት መረጃ አስተዳደር ስርዓትና ኣይ ሲ ቲ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰብስቤ ለማ የዲጂታል ስርዓቱ ጥራት፣ ተዓማኒነትና ወቅታዊነት ያለው መረጃን ወጥነት ባለው መልኩ ለማሰባሰብ፣ ለማደራጀትና ለመተንተን የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ዲጂታል ስርዓቱ ከዚህ በፊት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የነበሩትን የመረጃ አሰባሰብ፣ አተናተንና አስተዳደር ችግሮችን በላቀ ደረጃ የሚፈታ መሆኑንም አቶ ሰብስቤ ተናግረዋል።

የዲጅታል ስርዓቱ ሁሉንም በሀገሪቱ ያሉ የመንግስትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መረጃዎችን በአንድ ቋት አደራጅቶ ለሚፈለገው አላማ በግብዓትነት ለማዋል የሚያስችልና ለአጠቃቀም ቀላልና ቀልጣፋ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ለሚመለከታቸው የግልና የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አካላት በአዲሱ ዲጂታል ስርዓት አጠቃቀምና አስተዳደር ዙሪያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተስጥቶ ወደ ተግባር መገባቱንም አመልክተዋል።

በውይይቱም ከሁሉም የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ አግባብነት ያላቸው ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ከትምህርት ሚኒስቴር ይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም