የዳኝነት ስርዓቱን በማሻሻል የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የዳኝነት ስርዓቱን በማሻሻል የዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት ይሰራል
ጥር 15/2015 /ኢዜአ/ የዳኝነት ስርዓቱን በማሻሻል ለዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ በቂ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት ገለጹ።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት እና ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አበባ እምቢአለ ከቀድሞው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ ኃላፊ ጋር የስራ ርክክብ አድርገዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምሕረት፤ የቀድሞው የስራ ኃላፊዎች የፍርድ ቤቱን ተቋማዊ የዳኝነት ስርዓት ለማሻሻል ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ፍርድ ቤቶች የቆዩ እና የተጠራቀሙ ችግሮችን የተሸከሙ ተቋማት መሆናቸውን ጠቁመው፤ ቀጣይ የዳኝነት ስርዓቱን በማሻሻል ለዜጎችን የፍትሕ ጥያቄ በቂ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በሕዝብ ፍላጎትና በአገልግሎት አቅርቦት መካከል የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላትም በቴክኖሎጂ የታገዙ አዳዲስና ቀልጣፋ የዳኝነት ስርዓቶች ተግባራዊ ይሆናሉ ብለዋል።
በሕዝቦች ዘንድ እምነት የተጣለበት የዳኝነት ስርዓት እንዲኖርም የተገልጋይን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት በትኩረት ይሰራልም ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።
ሕብረተሰቡም የዳኝነት የአሰራር ሂደት የሚጠይቀውን ጊዜ እና የአሰራር ሂደት ከግምት በማስገባት ለሚሰጡ ምላሾች እና ለሚወሰዱ እርምጃዎች ትብብር እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
የፍትሕ ተቋማት የአገረ መንግስት አምድና የአገር ህልውና መሆናቸውን በመገንዘብ የፍርድ ቤቶችን ነፃነት በማረጋገጥ ተጠያቂነት እንዲሰፍን በሚደረገው ጥረት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም አቶ ቴዎድሮስ አሳስበዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የቀድሞ ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ፤ "የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት አገራችንን እንድናገለግል ለሰጠን እድል ምስጋና እናቀርባለን" ሲሉ ገልጸዋል።
የዳኝነት ስርዓቱን ለማሻሻል በተደረገ ጥረት ባለፉት አራት ዓመታት ተቋማዊ የማሻሻያ እርምጃ በመውሰድ ነፃና ቀልጣፋ የዳኝነት አገልግሎት በመስጠት "ውጤታማ" ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በዚህም የዳኝነት ስርዓቱን ቀልጣፋና ፈጣን ያደርጋሉ ተብሎ የታመነባቸው የሕግ ማዕቀፎች ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉን አመልክተዋል።
ከሰሞኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ አቶ ቴዎድሮስ ምህረትን የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ወይዘሮ አበባ እምቢአለን ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ መሾሙ ይታወሳል።
በስራ ኃላፊነት ርክክብ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ እንዲሁም ሌሎች የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።