ቀጥታ፡

በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደረቅ፣ ፀሀያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2015 በሚቀጥሉት 11 ቀናት በአብዛኛው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ደረቅ፣ ፀሀያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ የሚጠበው ሲሆን ቀዝቃዛማው የአየር ሁኔታ እየቀነሰ የሚመጣ መሆኑንም የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት በቀጣዮቹ ቀናት በመላ ኢትዮጵያ የሚስተዋለውን የአየር ሁኔታ በማስመልከት ለኢዜአ መግለጫ ልኳል፡፡

በመግለጫውም እንዳመለከተው በሚቀጥሉት 11 ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደረቅ፤ ፀሀያማና ነፋሻማ የአየር ፀባይ ይጠበቃል ብሏል።

በደጋማ አካባቢዎች በማለዳና በሌሊት ሲስተዋል የነበረው ቀዝቃዛማ የአየር ሁኔታ እየቀነሰ የሚሄድ መሆኑን አስታውቋል።

በደቡብ ምዕራብና በሰሜን ምስራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ መጠነኛ የደመና ሽፋን የሚስተዋል መሆኑንም ጠቅሷል።

በዚህም በደቡብ ምዕራብና ጥቂት የሰሜን ምስራቅ እና ምስራቅ የሀገሪቱ ክፍሎች በቀጣዮቹ ቀናት ቀላልና መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ ይጠበቃል ብሏል።

በሰሜን ምዕራብ፤ የደቡብ ምስራቅና የመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ደግሞ ደረቅ ፀሃያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ እንደሚስተዋል በመጠቆም የአየር ሁኔታው ለሰብል ስብሰባ አመቺ ነው ተብሏል።

በአንጻሩ በደጋማ አካባቢዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ እየቀነሰ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የግብርና ስራዎችን ለማከናወን ይጠቅማል ተብሏል።

በተጨማሪም በደቡብ ምዕራብ፤በጥቂት የሰሜን ምስራቅ እና ምስራቅ የሀገሪቱ ቦታዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

በመሆኑም በእነዚህ አካባቢዎች ለቋሚ ተክሎች እና የተለያዩ የፍራፍሬ ተክሎች ጠቃሚ መሆኑ ተመላክቷል።

የበልግ ወቅት እርሻን አስቀድመው ለሚጀምሩ አካባቢዎችም የማሳ ዝግጅት ለማከናወን ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ተብሏል።

የሰሜን ምስራቅ፣ የመካከለኛው እና የምስራቅ የሀገሪቱ ተፋሰሶች በአብዛኛው ደረቅ እና ከፊል ደረቃማ የአየር ሁኔታ የሚኖራቸው መሆኑን የኢንስቲትዩቱ መረጃ ያመለክታል።

የኦሞ ጊቤ፣ የላይኛው ባሮ አኮቦ፣ ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች ላይ መጠነኛ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም