ቀጥታ፡

ከ218 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች ተያዙ-ጉምሩክ ኮሚሽን

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2015 የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ከ218 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መያዛቸውን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ከጥር 5 እስከ 11 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ከ142 ነጥብ 6 ሚሊዮን የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 75 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር የወጭ እቃዎች ተይዘዋል።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት፣ ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት ድሬድዋ፣ አዋሽ እና ጅግጅጋ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 61 ነጥብ 6 ሚሊዮን፣ 22 ነጥብ 3 ሚሊዮን እና 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ እቃዎችን መያዝ ችለዋል፡፡

ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ ዘጠኝ ግለሰቦች እና ስምንት ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን ተጽእኖ ለመከላከል ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን እንዲወጣ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም