ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ እያገዙ ነው - የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት - ኢዜአ አማርኛ
ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ እያገዙ ነው - የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት
ሻሸመኔ ጥር 15/15 /ኢዜአ/ ባሕላዊ ፍርድ ቤቶች ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ እያገዙ መሆናቸውን የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከኦሮሚያ ባህልና ቱርዝም ቢሮ ጋር በመተባባር የባህላዊ ፍርድ ቤት ዓመታዊ ጉባኤ በሻሸመኔ ከተማ አካሄዷል።
በውይይቱ ላይ የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ገዛሊ አባሲመል እንደተናገሩት፣ ባህላዊ ፍርድ ቤቶቹ የሚያጋጥሙ ግጭቶች በመፍታት ረገድ ውጤት እያመጡ ነው።
ፍርድ ቤቶቹ ግጭቶችና አለመግባባቶችን በመፍታት እርቅና ሰላም እንዲወርድ በማድረግ የሕዝቡን አንድነት እያጠናከሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ማህበረሰቡ በራሱ ባሕል፣ ስርዓትና ዕሴት ጉዳዮቹ ታይቶ በአካባቢው ባህልና ወግ መሰረት ውሳኔ እያገኘ መሆኑንም ገልጸዋል።
በተለይ ደግሞ ጉዳዩ በማህበረሰቡ ባሕልና ዕሴት መሰረት ስለሚስተናገድ ፍትሕ እንዳይዛባ ዕድል መፍጠሩንም ጠቅሰዋል።
ባለፉት ስድስት ወራት ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር አመርቂ ስራ መሰራቱን የገለፁት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህም ከ100 ሺህ በላይ የሚሆኑ ጉዳዮች በዚሁ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማግኘታቸውንም አመላክተዋል።
በክልሉ ከ6 ሺህ በላይ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ተቋቁመው እየተሰራባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
ወደፊትም የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፣ በዚህም ለፍርድ ቤቶቹ የሚውል ቢሮና ሌሎች አገልግሎቶች ለማሟላት እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
የኦሮሚያ ክልል በህልና ቱርዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሁሴን ፈይሶ በበኩላቸው፣ ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን ተመልክተው ውሳኔ ከሰጡ በኋላ ሁለቱን አካላት አስታርቀው ሰላም እንዲወርድ እያደረጉ ነው ብለዋል።
ይህም በማህበረሰቡ መካከል መቻቻል፣ ፍቅርና ወንድማማችነት የበለጠ እንዲጠናከር ትልቅ አስታዋጽኦ እያበረከተ እንደሆነም አመላክተዋል።
የኦሮሚያ አበገዳዎች ሕብረት ሰብሳቢ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ኢሬሶ በበኩላቸው ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ሕዝቡ የአካባቢውን ባህልና እሴት እንዲሁም ቋንቋውን በሚያውቁ ሽማግሌዎች ስለሚዳኝ በዕምነት፣ በሀብት፣ በዘርና በጎሳ ሳይለያይ ፍትሕ እንዲያገኝ ያስችላሉ ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ባለ ጉዳዮች መካከል ቂምና ቁርሾ እንዳይኖር ስለሚረዳ ውሳኔንና እርቅን አጣምሮ ዘላቂ ሰላም እንዲስፍን ያግዛል ነው ያሉት።
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ሕብረተሰቡ በአካባቢው በሚያውቃቸውና በሚያውቁት አባ ገዳዎች፣ ሃዳ ሲንቄዎችና በአገር ሽማግሌዎች መዳኘቱ ፍትህን በቅርበት እንዲያገኝ አስችሎታል ያሉት ደግሞ አባገዳ ጉግሳ ኢብሳ ናቸው።
በዘመናዊ ፍርድ ቤቶች ለመዳኘት የሚወጣውን ወጪ ስለሚያስቀርም ጥቅሙ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አባገዳ ቃሲም ሐጂ ጆንጃ በበኩላቸው ባህላዊ ፍርድ ቤቶች በማህበረሰቡ ባሕልና ዕሴቶች መሰረት ስለሚያስተናግዱ ማህበረሰቡ የፍትሕ መዛባት 'ያጋጥመኛል' ከሚል ስጋት ነጻ ያደርጋልና ጠቀሜታው የላቀ ነው ብለዋል።
ባህላዊ ፍርድ ቤቶች ከዘመናዊው ፍርድ ቤቶች ጋር ተናበው እንዲሰሩ መደረጉ ደግሞ ለማሕበረሰቡ ተጨማሪ ጥቅም አስገኝቷል ነው ያሉት።
በተጨማሪም ፍርድ ቤቶቹ ይደርስ የነበረውን እንግልት ከማስቀረቱም በላይ በጉዳይ አስፈጻሚዎች እንዳይጨበረበሩ ምቹ እድል መፍጠሩን ገልጸዋል።
የክልሉ ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 240/2013 ለባህላዊ ፍርድ ቤቶች ህጋዊ እውቅና መስጠቱ ይታወሳል።