የምስራቅ አፍሪካ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው

187

ዲላ (ኢዜአ) ጥር 15/2015 የምስራቅ አፍሪካ የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የደቡብ ክልል 20ኛው የባህል ስፖርቶች ውድድርና 16ኛው የስፖርት ፌስቲቫል በዲላ ከተማ ዛሬ ተጀምሯል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሚኒስቴር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ባህላዊ ስፖርቶችና ፌስቲቫሎች የሀገርን ገጽታ የማጎላት እና የሕዝቦችን ትስስር በማጠናከር ረገድ ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

ይሁንና ዘርፉን አልምቶና ተንከባክቦ ለሀገራዊ እድገት ከመጠቀም አንጻር ውስንነቶች አሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ በውስጧ ያሉትንና የጎረቤት ሀገራትን የባህል ስፖርቶች በማወዳደር ሃብቱን ለማልማትና ለመጠቀም እየሰራች እንደሆነ ተናግረዋል።

ቀጠናውን ሊያስተሳስር የሚችል የምስራቅ አፍሪካ የባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫሎች ውድድር ለ”መጀመሪያ ጊዜ” እንደሚካሄድ ነው አምባሳደር መስፍን የጠቆሙት።

ውድድር እና ፌስቲቫሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ከጥር እስከ መጋቢት ወር 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ እንደሚከናወን አመልክተዋል።

የተወሰኑ የዝግጅት ስራዎች እና የተሳታፊ አገራትን የመለየት ተግባር በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል።

በሌላ በኩል የደቡብ ክልል ከፍተኛ የባህል ስፖርቶች ሃብት ያለበት አከባቢ ነው ያሉት አምባሳደር መስፍን የውድድሩ ተሳታፊዎች ወንድማማችነትን ማጎልበት እና በምስራቅ አፍሪካው ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው ለመሳተፍ ጠንካራ ፉክክር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዴላሞ ኦቶሬ የክልሉ መንግስት ስፖርቱን ለማልማት በተለይ የባህል ዘርፉን ለማስተዋወቅና ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

የወድድሩ ተሳታፊዎችም ስፖርታዊ ጨዋነትን መሰረት ያደረገ ፉክክር ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

ለዘጠኝ ተከታታይ ቀናት በሚካሄደው የባህል ስፖርቶች ውድድር እና ፌስቲቫል በዘጠኝ የስፖርት አይነቶች በደቡ ክልል ከሚገኙ ዞኖች እና ወረዳዎች ከ1 ሺህ 200 በላይ ስፖርተኞችና ልዑካን እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም