አየር ንብረት ለዉጥን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት የተቀናጀ ተፋሰስ ስራ መደገፍ አለበት - ኢዜአ አማርኛ
አየር ንብረት ለዉጥን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት የተቀናጀ ተፋሰስ ስራ መደገፍ አለበት
ሀላባ /ኢዜአ/ 15/2015 አየር ንብረት ለዉጡን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት በተቀናጀ ተፋሰስ ስራ መደገፍ እንደሚገባ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትር ዲኤታው ፕሮፌሰር ኢያሱ ኤሊያስ በደቡብ ክልል የተፋሰስ ልማት ማስጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልእክት በበጀት ዓመቱ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በተፋሰስ ይለማል ብለዋል።
የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ዘላቂነት ለማረጋገጥ አፈርን በማሳ የማቆየት መርህን በተከተለ መልኩ ህብረተሰቡን የተፋሰሱ ባለቤት ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ፣በተቀናጀ ተፋሰስ ልማት፣በአትክልት ልማት ዘርፍ ያለውን ተሞክሮ በሌሎች ክልሎች ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።
የደቡብ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በበኩላቸው የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግ የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ስራው በትኩረት እንደሚከናወን ተናግረዋል።
ርእሰ መስተዳድሩ ክልል አቀፉን የተቀናጀ ተፋሰስ ስራ በሀላባ ዞን ሲያስጀምሩ እንደተናገሩት በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወነው ስራ በተጨባጭ ውጤት አምጥቷል።
የተፋሰስ ስራው የወንዞችን መዳረሻ በመለየት የአካባቢውን ህብረተሰብ የማሳተፍ ስራ በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ ስራው በተመረጡ ተፋሰሶች በተቀናጀ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በበጀት ዓመቱ በ293ሺ640 ሄክታር መሬት በተፋሰስ ስራው እንደሚለማ ታውቋል።