ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ለ60 ቀናት የሚቆይ የተፋሰስ ልማት ተጀመረ

ጥር 15/2015 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የዘንድሮው የተፋሰስ ልማት ስራ በምስራቅ ሸዋ ዞን በአዳማ ወረዳ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርጫፍ የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በተገኙበት ተጀምሯል ።

በማስጀመሪያ መረሃ ግብሩ ላይ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ እንደገለፁት ባለፉት ዓመታት የተሰሩት የተፋሰስ ልማት ስራዎች በግብርና ምርትና ምርታማነት መጨመር ላይ ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ነው ብለዋል ።

May be an image of 2 people and outdoors

በተለይ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በመደገፉ የተራቆቱ መሬቶች እንዲያገግሙ የደረቁ ወንዞችና ዥረቶች እንዲመለሱ ማስቻሉንም ተናግሯል ።

በዚህም በክልሉ የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር ውሃ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ጠቀስው የአርሶ አደሩን የስራ ባህል የለወጠ ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል ።

May be an image of 7 people, people standing, outdoors and tree

“የአዋሽ ተፋሰስና የአዋሽ ወንዝ የኢትዮጵያ እስትንፋስ ነው” ያሉት ዶክተር ቢቂላ በማዕከላዊ የኦሮሚያ ዞኖች ላይ የሚሰሩ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ የአዋሽ ወንዝ የውሃ መጠን እንዲጨምር ከማድረጉም ባለፈ ለበጋ ስንዴና ለአጠቃላይ የመስኖ ልማት ስራ በቂ ውሃ እንድናገኝ ያስችላል ነው ያሉት ።

በዚህም ህዝቡ የጀመረውን አካላዊ የአፈርና ውሃ ዕቀባ በአረንጓዴ አሻራ ፕሮግራም በማስደገፍ የተተከሉትን በመንከባከብና ለመጪው ክረምት ችግኞችን በማዘጋጀት የተቀናጀ ተግባር ማከናወን እንደሚገባው አስገንዝበዋል ።

የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው በዞኑ ባለፉት ዓመታት በተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች አንድ ጊዜ ብቻ ሲያመርቱ የነበሩ አርሶ አደሮች በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ ማምረት መጀመራቸውን ተናግረዋል ።
በተጨማሪም የአርሶ አደሩን የስራ ባህል እየተለወጠ መሆኑን ጠቅሰው ከመደበኛ ዝናብ ባለፈ በቂ ውሃ የሌለበት የምስራቅ ሸዋ ዞን በአሁኑ ወቅት በዓመት እስከ ሶስት ጊዜ እንዲያመርት በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ላይ የተሰሩ ስራዎች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል ።
የምስራቅ ሸዋ ዞን የግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ በበኩላቸው በዞኑ 60 ቀናት በሚቆየው የተፋሰስ ልማት ስራ በ291 ተፋሰሶችን ላይ የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ዕቀባ ስራ እንደሚካሄድ ተናግረዋል ።
በተጨማሪም ከተፋሰስ ልማቱ ጎን ለጎን ባለፈው ክረምት የተተከሉትን ችግኞች የመንከባከብ ስራ ይሰራል ነው ያሉት


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም