በቻን ውድድር ሱዳን ከማዳጋስካር ይጫወታሉ

16

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 15/2015 በሰባተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) ሱዳን ከማዳጋስካር ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት እና በአልጄሪያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የቻን ውድድር ዛሬ 11ኛ ቀኑን አስቆጥሯል።

በምድብ ሶስት ከምሽቱ 4 ሰአት 40 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ሞሐመድ ሃምላዊ ስታዲየም ሱዳን ከማዳጋስካር ይጫወታሉ።

ማዳጋስካር ጋናን 2 ለ 1 በማሸነፍ እንዲሁም ሞሮኮ ከውድድሩ ራሷን ማግለሏን ተከትሎ የ3 ለ 0 እና የሶስት ነጥብ ፎርፌ ውጤት አግኝታለች።

የደሴቲቷ አገር ምድቡን በስድስት ነጥብ እና በአራት የግብ ክፍያ እየመራች ነው።

በአንጻሩ ተጋጣሚዋ ሱዳን በጋና 3 ለ 1 ተሸንፋ እንዲሁም ከሞሮኮ ባገኘችው የ3 ለ 0 እና የሶስት ነጥብ የፎርፌ ውጤት አማካኝነት በሶስት ነጥብ እና በአንድ የግብ ክፍያ ሶስተኛ ደረጃን ይዛለች።

ማዳጋስካር ማሸነፍ እና አቻ መውጣት ወደ ሩብ ፍጻሜ ያሳልፋታል።
ሱዳን ወደ ሩብ ፍጻሜው ለመግባት ማዳጋስካርን ከሁለት እና ከዚያ በላይ የግብ ልዩነት ማሸነፍ አለባት።

በምድብ አንድ ጋና በስድስት ነጥብ እና በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

በተያያዘ ዜና ትናንት በቻን ውድድር በምድብ ሁለት በተደረጉ ጨዋታዎች ሴኔጋል ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን 3 ለ 0 እንዲሁም ኮትዲቭዋር ዩጋንዳን 3 ለ 1 አሸንፈዋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሴኔጋል በስድስት ነጥብ፤ ኮትዲቭዋር በአራት ነጥብ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃን ይዘው ወደ ሩብ ፍጻሜው ገብተዋል።

በአንጻሩ የሁለት ጊዜ የቻን አሸናፊ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከውድድሩ ተሰናብታለች።
የቻን ውድድር የምድብ ጨዋታዎች ነገ ይጠናቀቃሉ።

አራት አገራት ባሉባቸው ምድቦች አንደኛ እና ሁለተኛ የወጡ እንዲሁም ሶስት አገራት ባሉባቸው ምድቦች የምድቡ አሸናፊ ወደ ሩብ ፍጻሜ ያልፋሉ።

የሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች ጥር 19 እና 20 ቀን 2015 ዓ.ም ይካሄዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም