በህገወጥ መንገድ የገቡ እቃዎችን ለማሳለፍ የሞከሩ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ - ኢዜአ አማርኛ
በህገወጥ መንገድ የገቡ እቃዎችን ለማሳለፍ የሞከሩ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ሰራተኞች በቁጥጥር ስር ዋሉ
ጥር 15/2015 (ኢዜአ) የተሰጣቸውን ኃላፊነት ወደጎን በመተው በህገወጥ መንገድ የገቡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን ለማሳለፍ የሞከሩ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ሰራተኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ኤርፖርት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ክትትል እና ቁጥጥር እንዲያደርጉ የተመደቡ የህብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ሰራተኞች ከውጭ ገቢ መንገደኞች የኮንትሮባንድ እቃን በመረከብ እና ደብቀው ለማሳለፍ ሲሞክሩ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኤርፖርት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ጥር 12 እና 13 2015 ዓ.ም ባደረገው ክትትል ከመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ሽፋን በማድረግ 42 ዘመናዊ የእጅ ስልኮች እና በርካታ የስማርት ስልክ ቦርድ ስክሪኖችን በቦርሳ በመደበቅ ይዘው ለመውጣት የሞከሩ ሁለት የኢንስቲትቱ ሰራተኞች በቁጥጥር ስር አውሏል።
በአዲስ አበባ ኤርፖርት ህገወጥ የገንዘብ ዝውውር ፣ የከበሩ ማዕድናት፣ የአደንዛዥ እጽ ዝውውር እና ሌሎች መሰል ወንጀሎች በተደጋጋሚ እየተስተዋሉ በመሆኑ ተቋማትን በመወከል የሴኩሪቲ መግቢያ ፈቃድ መታወቂያ ይዘው በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ጉምሩክ ኮሚሽን ከወትሮው በተለየ ጥብቅ ፍተሻ የሚያደርግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ይገልጻል።
ኮሚሽኑ በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ ለአዲስ አበባ ኤርፖርት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አመራሮች እና ሰራተኞች ምስጋናውን ያደርሳል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪው አቅርቧል፡፡