የዓባይን ወንዝ መነሻን በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ትኩረት እንደሚሻ ተመለከተ - ኢዜአ አማርኛ
የዓባይን ወንዝ መነሻን በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ትኩረት እንደሚሻ ተመለከተ

ባህር ዳር፤ ጥር 14ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- የዓባይን ወንዝ መነሻ አካባቢውን በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ትኩረት እንደሚሻ ተመለከተ።
5ኛው የግዮን በዓልና የፃድቁ አቡነ ዘርዓብሩክ ዓመታዊ ክብረ በዓል በታላቁ ዓባይ ወንዝ መነሻ ሰከላ ግሽ ዓባይ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በበዓሉ የተገኙት የብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ እንዳሉት፤ የዓባይ ወንዝ ምንጭ/መነሻ/አካባቢ የኢትዮጵያን ስነ-ተፈጥሮአዊ ሚስጢራትና የማይቋረጥ የረጅም ጊዜ ታሪክ ባለቤት መሆኗን የሚያሳይ ነው።
በየአካባቢው እምቅ የሆኑ የቱሪዝም ሃብቶች ቢኖሩም የግዮን/ዓባይ/ ምንጭ የሆነውን አካባቢ ማልማትና ለዓለም የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ማድረግ መቻል የተለየ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል።
ዓባይ የኢትዮጵያዊያን የታሪክ ገናናነት ማሳያ፤ ዛሬ ላይ ደግሞ በራስ አቅምና እውቀት ተገድቦ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ከግምት በማስገባት ሃይል በማመንጨት ደረጃ ላይ በመሆኑ በዓሉን በልዩነት ያደምቀዋል ብለዋል።
የዓባይ ወንዝ ምንጭ/መነሻ / አካባቢን ለማልማትና ለማበልጸግ ሁሉን አቀፍ ስራ የሚጠይቅና የሁሉንም ርብርብ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።
አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የምርምርና የልማት ስራዎች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው፤ ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ስራ በስፋት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
መንግስት አካባቢውን ለማልማት ለሚሳተፉ አካላት ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጸዋል።

የዓባይን ወንዝ መነሻ አካባቢውን በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ ናቸው።
መንግስት አካባቢው የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን በማሰብ በዓሉን ማክበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለውጦች እየታዩ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንን በመደገፍ አካባቢውን ማልማትም የሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ትኩረት እንደሚሻ አመልክተዋል።
በአካባቢው ልማት ለማልማት ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።

የምእራብ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶድ አባል ብፅዑ አቡነ ዘካሪያስ በበኩላቸው፤ ''ዓባይ ለኢትዮጵያዊያን መንፈሳዊም ስጋዊም ሃብታቸው ነው'' ሲሉ ገልጸዋል።
ዓባይ ከኢትዮጵያ አልፎ ለሌሎች ዓለማትም ተስፋና ምግብ የሆነ ወንዝ መሆኑን ጠቅሰው፤መነሻውን ለማልማት በተባበረ መንገድ መረባረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በበዓሉ ስነ-ስርዓት የክልሉ፣ የዞንና የወረዳ የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች መታደማቸው ታውቋል።