ቀጥታ፡

ኦሞ ባንክ ውዝፍ እዳውን በማስመለስ ለማህበራት የፋይናንስ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ነው

ዲላ ጥር 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) በደንበኞች እጅ የሚገኝ ውዝፍ እዳን በማስመለስ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች የፋይናንስ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየሠራ መሆኑን የኦሞ ባንክ አክስዮን ማህበር ገለጸ ። 

ባንኩ በዲላ ከተማ በካሄደው የግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ የተለያዩ ውሳኔዎችን ማስተላለፉንም ገልጿል። 

የኦሞ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አለማየሁ ሃይለጊዮርጊስ እንደተናገሩት፤ ባንኩ የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት በግንባር ቀደምትነት እየሠራ ነው። 

በተለይም በሁሉም አከባቢዎች ለሚገኙ ማህበራትና ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ ጥያቄ ቅድሚያና አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ከቅርንጫፍ ሃላፊዎችና ከባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል። 

ባንኩ የኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ዜጎች የሥራ አጥነት ችግር በመፍታት የኢኮኖሚ ተጠቃሚ የማድረግ ሃላፊነቱን በጽኑ እንደሚወጣም አስረድተዋል።  

የባንኩ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ እጅጉ አንግሶ በበኩላቸው፤ ባንኩ ባለፉት ስድስት ወራት በቁጠባ መጠንና በብድር ስርጭት የተሻለ ውጤት አስመዝግቧል። 

ይሁንና በደንበኞች እጅ የሚገኝ ውዝፍ ዕዳ አሁንም ተግዳሮት መሆኑን አንስተው፤ እስከዛሬ በደንበኞች እጅ ከ7 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ውዝፍ እዳ መኖሩን ገልጸዋል። 

በግማሽ ዓመቱም ብድር ለማስመለስ በተደረገ ጥረት ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ማስመለስ ቢቻልም ከእቅድና ከብድር ፍላጎት አንጻር አሁንም ዝቅተኛ አፈጻጸም መሆኑን አስረድተዋል። 

ያንን በተሻለ ለማከናወን የውዝፍ እዳ አስመላሽ ግብረሃይል በመቋቋም በተለይም በዋስትና የተሰጡ ብድሮችን ባንኩ በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የማስመለስ ሥራ እየከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ውዝፍ እዳውን የማስመለሱ ሥራ ተጠናክሮ በቀጠለ መጠን በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች የፋይናንስ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አቅም እንደሚሆናቸውም ገልጸዋል። 

በተለይም ተቋሙ ከብድርና ቁጠባ ወደ ባንክ ማደጉ በብድር ጣራ ምክንያት ተጠቃሚ መሆን ያልቻሉ ማህበራትንና ኢንተርፕራይዞችን ለመደገፍ አቅም እንደሚያስገኝለት አስረድተዋል።  

ባንኩ ከከተሞች ባለፈ በገጠር የወጣቶቹንና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማስፋት ከ700 በላይ ክላስተሮችን በማቋቋም አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም አስረድተዋል።

 ህዝባዊ መሰረት ያላቸውን የቁጠባ ምንጭች ለመለየት በተደረገ ጥረት በስድስት ወር ውስጥ ብቻ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ቁጠባ መሰብሰብ መቻሉን ያነሱት ደግሞ በኦሞ ባንክ የሶዶ ዲስትሪክት ስራ አስኪያጅ አቶ ተመስገን ያይና ናቸው።  

በዚህም የወጣቶችና የሴቶች ተሳትፎ የላቀ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከቁጠባ ባለፈ በብድር ስርጭትና ማስመለስ በተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ከ53 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ መገኝቱንም አስረድተዋል። 

በዲስትሪክቱ ስር በሚገኙ 24 ቅርንጫፎችም ዝቅተኛውን መስፈርት አሟልተው የፋይናንስ ጥያቄ ለሚያቀርቡ ወጣቶች በተፋጠነ ሁኔታ በ5 ቀናት ውስጥ ምላሽ እየተሰጠ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

  በመድረኩም የክልልና የዞን ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች የባንኩ ዲስትሪክትና የቅርንጫፍ ሃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም