ነዋሪዎቹ ከኢህዴግ ጉባዔው ሰላምናና ዴሞክራሲን የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን እንደሚጠብቁ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ነዋሪዎቹ ከኢህዴግ ጉባዔው ሰላምናና ዴሞክራሲን የሚያረጋግጡ ውሳኔዎችን እንደሚጠብቁ ገለጹ
ጊምቢ መስከረም 23/2011 በኦሮሚያ ክልል የጊምቢ ከተማ ነዋሪዎች ከ11ኛው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኢህአዴግ) ጉባዔ ሰላምና ዴሞክራሲን የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንደሚጠብቁ ተናገሩ፡፡ ከከተማዋ ነዋሪዎች መካከል አቶ መኮንን ዲነግዴ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢህአዴግ ከዛሬ ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ በሚያካሄደው ጉባዔ ሰላምን የሚያሰፍኑና ዴሞክራሲን የሚያጎለብቱ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብለው ይጠብቃሉ። ጉባዔው የአገሪቱን ዜጎች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እንደሚተላለፉበትም እምነታቸው ነው። የአገር ሽማግሌው አቶ አበራ የማነ ኢህአዴግ እያካሄደ ባለው ጉባዔ የተጀመረው የሰላምና ዴሞክራሲ ጉዞ ፍሬ የሚያፈራባቸውን ውሳኔዎች ማሳለፍ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ጉባዔው በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚሰሙትን የሰው ህይዎት መጥፋት፣ የአካል መጉደል፣የንብረት መውደምና የመፈናቀል አደጋ ለመቀነስና ብሎም ለማጥፋት የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን እንደሚያስተላልፍ ይጠብቃሉ። ሌላው የከተማዋ ነዋሪ አቶ አብርሃም ዲቢሳ በበኩላቸው ጉባዔው የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች የአገሪቱን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብትና ፍትሃዊ የምጣኔ ሃብት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ መሆን እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡ "አገራዊ አንድነት፤ለሁለንተናዊ ብልጽግና!”በሚል መሪ ቃል በሃዋሳ ከተማ ዛሬ የተጀመረው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ዛሬን ጨምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ይካሄዳል፡፡