በአማራ ክልል የመሬት ሀብትን በቴክኖሎጂ ታግዞ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የመሬት ሀብትን በቴክኖሎጂ ታግዞ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ደሴ (ኢዜአ) ጥር 13/2015 በአማራ ክልል ያለውን የመሬት ሀብት በቴክኖሎጂ ታግዞ በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን የአማራ ክልል መሬት ቢሮ አስታወቀ።
በደሴ ከተማ የሚስተዋለውን ህገ-ወጥ የመሬት ወረራና የቤት ግንባታን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር ተካሂዷል።
የአማራ ክልል መሬት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰይፉ ሰይድ እንደገለጹት፣ በክልሉ የወልና የመንግስት መሬት ላይ ጭምር ህገ-ወጥ ግንባታ እየተባባሰ መጥቷል።
ችግሩን ለማቃለል በቴክኖሎጂ ጭምር ታግዞ የክልሉን የመሬት ሀብት በአግባቡ ለመቆጣጠርና ለመጠቀም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ በክልሉ የሚገኙ 148 ወረዳዎችን ወደ ዘመናዊ የመሬት አስተዳደር ስርዓት ወይም ካዳስተር ለማስገባት በተደረገው ጥረት እስካሁን ድረስ 100 ወረዳዎችን ማስገባት ተችሏል።
በቀጣይ ሁለት ዓመታት ሁሉንም ወረዳዎች ወደ ካዳስተር ስርዓት አስገብቶ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።
የመሬት መረጃ በዘመናዊ መንገድ መመዝገብ ከተጀመረ ወዲህ ህገ-ወጥ ግንባታንና ከእሱ ጋር በተያያዘ የሚከሰት ሁከትን በመቀነስ በኩል ለውጥ መምጣቱንም ኃላፊው ተናግረው።
በክልሉ ካለው የእርሻ ማሳ ውስጥ 60 በመቶ ለሚሆነው የይዞታ ማረጋገጫ ደብተር መሰጠቱን አቶ ሰይፉ ጠቁመው፣ "በእዚህ በኩል የቀሩ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል" ብለዋል።
ሁሉም አሰራሩን በመደገፍ አጭበርባሪዎችን በመከላከል የየድርሻውን እንዲወጣም አሳስበዋል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር መሬት መምሪያ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ አድማሴ በበኩላቸው፣ በከተማው ያለውን የመሬት ሀብት አጠቃቀም ለማስተካከልና ብልሹ አሰራሮችን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
"ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ መበራከቱን ጠቁመው ችግሩን ለመከላል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው" ብለዋል።
በዚህም በየክፍለ ከተማ ያለውን የወልና የመንግስት መሬት የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ "በአንድ ክፍለ ከተማ ብቻ በተደረገ ጥናት ከ12 ሺህ ባለይ ይዞታዎች ውስጥ ትክክለኛ ሰነድ ያላቸው 9 ሺህ ብቻ ሲሆኑ ቀሪዎቹ የተጭበረበሩ ናቸው" ብለዋል።
በተለይ ደላሎች ከባለሙያ፣ ከፀጥታና ፍትህ አካላት ጋር ጭምር በመመሳጠር ዳግም ካሳ የማስከፈል፣ ክስ ሲመሰረትም የፍርድ ቤት እግድ የማውጣት ተግባር እንደሚፈጽሙ ገልጸዋል።
ከእዚህ በተጨማሪ የሚጠቀሙት ህገ-ወጥ ሰነድና ሌሎችም ተግዳሮቶች የዘርፉ ፈተና መሆናቸውን ነው አቶ ቴዎድሮስ ያስረዱት።
"በዘርፉ ያለውን ውስብስብ ችግር በማቃለል ህገ-ወጥ የመሬት ወረራውን ለመከላከልና ፍትህ ለማስፈን በቅንጅት ሥራ ጀምረናል" ያሉት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ጀንበሩ ካሳ ናቸው።
መሬትን በዘመናዊ መንገድ ለመያዝና ለመጠቀም ክልሉ የጀመረው ስራ መልካም መሆኑን ጠቁመው፤ "ሁሉም መሬት ወደ ዘመናዊ ስርዓት ገብቶ ችግሩ እስኪቃለል ድረስ ፍትህ እንዲሰፍን በቅንጅት እንሰራለን" ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አመራሮች እንዲሁም የፍትህና የፀጥታ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።