የዓባይ ወንዝ መነሻን በማልማት ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ይሰራል-አቶ ግርማ የሽጥላ

31

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥር 13/2015 የዓባይ ወንዝ መነሻን በማልማት ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ ገለጹ።

የግዮን በዓል 5ኛ ዓመትና የጻድቁ አቡነ ዘርዓብሩክ ዓመታዊ ክብረ በዓል በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የዓባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው ግሽ ዓባይ ከተማ ዛሬ ተከብሯል።

ሃላፊው አቶ ግርማ በሥነ ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ የዓባይ ወንዝ መነሻ በሆነችው ግሽ ዓባይ ከተማ የግዮን (ዓባይ ወንዝን) በዓል ማክበር የአንድነትና የመተባበር ተምሳሌትነትን የሚያጎላ ነው።

የዓባይ ወንዝ ከመነሻው ትንሽ ቢሆንም በርካታ ገባሮችን እያስተባበረ ሃያልና ገናና መሆን እንደቻለ የገለጹት አቶ ግርማ፣ "ይህም ኢትዮጵያውያንም ተባብረው በአንድነት መቆም ከቻሉ የማይወጡት ችግር እንደሌለ ማሳያ ነው" ብለዋል።

የዓባይ ወንዝ መነሻ በሆነው ቦታ ላይ በዓሉ መከበሩ በአፍሪካና በዓለም የሚታወቀውን ዓባይ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በማሰብ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።

"ዓባይ የኢትዮጵያውያን መገለጫና የነገ ተስፋቸው ስለሆነ የዓባይን መነሻ ለማልማት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል" ብለዋል።

የዘንድሮ የግዮን በዓል ከዚህ ቀደም ከነበሩት አከባበሮች እንደሚለይ የገለጹት አቶ ግርማ፣ መንግስት የዓባይን ወንዝ መነሻን በማልማት ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለም የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በትኩረት እንደሚስራ ገልፀዋል።

አካባቢውን ለማልማት ለሚመጡ ባለሃብቶች በክልሉ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግስት የዓባይ ወንዝ መነሻ ቦታን በማልማት የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እያከናወነ ባለው ሥራ አካባቢው እየተነቃቃ መጥቷል" ያሉት ደግሞ የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ተሾመ ናቸው።

"የዓባይ ወንዝ መነሻን አልምቶ የቱሪዝም መዳረሻ የማድረጉ ሥራ ለተወሰነ አካል ብቻ የሚተው ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያውያንን ትኩረት የሚሻ ነው" ብለዋል።

የዞኑ አስተዳደር ወደ አካባቢው መጥተው መዋዕለ ንዋያቸውን ለሚያፈሱ ባለሃብቶች ተገቢ ድጋፍ እንደሚያደርግም ዋና አስተዳዳሪው አክለዋል።

በበዓሉ ላይ የምዕራብ ጎጃም ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፅዕ አቡነ ዘካሪያስ፣ የክልልና የዞን የተለያዩ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም