ከኦሮሚያ ክልል ለውጪ ገበያ የሚቀርብ የስንዴ ምርት በሕብረት ስራ ማሕበራት በኩል ግዢ እንዲፈጸም እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ከኦሮሚያ ክልል ለውጪ ገበያ የሚቀርብ የስንዴ ምርት በሕብረት ስራ ማሕበራት በኩል ግዢ እንዲፈጸም እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ጥር 13/2015 /ኢዜአ/ ከኦሮሚያ ክልል ለውጪ ገበያ የሚቀርብ የስንዴ ምርት በሕብረት ስራ ማሕበራት በኩል ግዢ እንዲፈጸም እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።
በምዕራብ አርሲ ዞን ለውጪ ገቢያ የሚቀርበውን ስንዴ በሕብረት ስራ በኩል ማገበያየት በሚቻልበት ዙሪያ ከነጋዴዎችና ከሕብረት ስራ ማሕበራት ጋር ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በረሶ ፈይሳ እንደገለፁት፣ በክልሉ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በግብርና ልማት ዘርፍ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።
በተለይም በስንዴ ልማት ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱን ጠቅሰው የተመረተው ስንዴም በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት አልፎ ለውጪ ገበያ ሊቀርብ ይገባል ብለዋል።
በስንዴ ምርት ላይ በተከናወነ ስራ ምርትና ምርታማነቱ እንዲሁም የገበያ መዳረሻው እየሰፋ ስለሚሄድ በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መመራት አስፈላጊ ሆኖ ተገንቷል ነው ያሉት።
በዘመናዊ መንገድ መገበያየት የምርት ጥራትን የበለጠ በማሳደግ የግብይት ሥርዓቱ ሕጋዊ እንዲሆን ያስችላል ብለዋል።
ለዚህም ሲባል አርሶ አደሩ ለሕብረት ስራ ማሕበራት ስንዴ እንዲሸጥና የኢትዮጵያ ንግድ ሥራ ኮርፖሬሽን ደግሞ ከሕብረት ስራ ማሕበራት እንዲገዛ መደረጉን ጠቁመዋል።
በዚህም አርሶ አደሩ፣ አቅራቢውና ላኪው በአጠቃላይ አገር ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ያስችላል ብለዋል።
በዚህ በጀት ዓመት ከኦሮሚያ ክልል 15 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተስራ መሆኑንም አስታውሰዋል።
የምዕራብ አርሲ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ አህመድ ሐጂ በበኩላቸው ዞኑ ለስንዴ ምርት ከፍተኛ አቅም ያለው በመሆኑ ስንዴ በመደበኛ እና በበጋ በስፋት እየተመረተ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ዘንድሮ 2 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከዞኑ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተስራ መሆኑን ገልጸው የታቀደው እንዲሳካ በዞኑ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ ክትትል በማደረግ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ አመላክተዋል።
በዚህም በስድስት ወራት 3 ሺህ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንና በዚህም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግስት ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ ከተሳታፉ ነጋዴዎች መካከል አቶ ደበበ ሂንካና ገመዳ አሊ መንግስት በገበያ ውስጥ ያሉ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን መከላከል አለበት ብለዋል።
በስንዴ ግብይት ሂደት ውስጥ በህገ-ወጥ መልኩ ለመጠቀም የሚሞክሩ ነጋዴዎች መኖራቸውን ገልጸው መንግስት ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ጠይቀዋል።