ቀጥታ፡

በደቡብ ሱዳን አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ ያገኘው "ቴሌ-ሞባይል" የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ ግኝት ለማስፋት አዎንታዊ ሚና ይጫወታል - ዶክተር አንዷለም አድማሴ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 13/2015 በደቡብ ሱዳን አገልግሎት ለመስጠት ፍቃድ ያገኘው "ቴሌ-ሞባይል" የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሬ ግኝት በማስፋት አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወት የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዷለም አድማሴ ተናገሩ።

"የቴሌ ሞባይል ደቡብ ሱዳን" ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አንዷለም አድማሴ ኩባንያው በደቡብ ሱዳን አገልግሎት ለመጀመር የሚያስችል ፈቃድ አግኝቶ የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶክተር አንዷለም አድማሱ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ ተቋሙ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ሥራውን ሲጀምር ከኤም.ቲ.ኤን፣ ዘይንና ዲ.ጂ.ቴል በመቀጠል አራተኛው የቴሌኮም ኩባንያ ነው ብለዋል።

ኩባንያው በደቡብ ሱዳን ሥራ መጀመሩ ለኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኝ ገልጸው በቴሌኮም ዘርፍ ለሰለጠኑ ኢትዮጵያዊያን ባለሙያዎች የሥራ እድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

"የቴሌ-ሞባይል ደቡብ ሱዳን" የቢዝነስ አዋጭነት ጥናት በማካሄድ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመው፤ በቀጣይም ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ልምድ እንዲወስዱ ይደርጋል ነው ያሉት።

ኩባንያው ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ አገራትን በማስተሳሰር አህጉራዊ የቴሌኮምዩኒኬሽን ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚሰራም ነው ያስረዱት።

ኢትዮጵና ደቡብ ሱዳን ሰፊ የሕዝብ ቁርኝት ያላቸው አገራት በመሆናቸው ኢትዮጵያን ወክሎ በደቡብ ሱዳን ኢንቨስት ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የቴሌኮም ዘርፉን ለማነቃቃት ያደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናን በቴሌኮም መሰረተ-ልማት ለማስተሳሰር እንደሚረዳም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም