የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል-አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

27

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 13/2015 የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችሉ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።  

በተለይም አሁን በአገሪቱ ያለውን የሠላም ሁኔታና ሌሎች ጉዳዮችን የማስተዋወቅና ተገቢውን ግንዛቤ መፍጠር የሚያስችሉ የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆናቸውን ነው ያስረዱት።  

ለዚህም በዋነኝነት በውጭ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች፣ በአገር ውስጥ የተለያዩ ተቋማት፣ ግለሰቦች እንዲሁም በፓርላማው በኩል የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።  

በዚህም የኢትዮጵያን ገጽታ በማስተዋወቅ መንግሥት ከመንግሥት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነት ውጤታማ በማድረግ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በተለይም በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወተው የፓርላማ ዲፕሎማሲ ግንኙነትን ከተለያዩ የዓለም አገራት ጋር ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ።

ይህም ከተለያዩ አገራት ጋር የፓርላማ የወዳጅነት ኮሚቴዎችን መፍጠር በስፋት እንደሚቀጥል ነው ያስረዱት። 

እንደ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጻ፤ በፐብሊክ ዲፕሎማሲው ዘርፍ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ምጣኔ ሃብታዊ፣ ባህላዊ፣ ወታደራዊና ሌሎች ጥቅሞችን ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።  

የአገርን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ሁሉም በየደረጃው በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ማሳወቅ ተገቢ መሆኑንም ገልጸዋለ። 

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮያውያን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የእምነት ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች የአገርን ጥቅም ማዕከል ያደረገ ሥራ ማከናወን እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል። 

በአፍሪካ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር የሚከናወኑ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ተግባራትም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አምባሳደር ዲና አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም