በሐረሪ ክልል ለታላቁ የኢትዮዽያ ሕዳሴ ግድብ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል ለታላቁ የኢትዮዽያ ሕዳሴ ግድብ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ
ሐረር (ኢዜአ) ጥር 12/2015 በሐረሪ ክልል ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የክልሉ የሕዳሴው ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮችና የሕዳሴው ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሄኖክ ሙሉነህ እንዳሉት፣ በክልሉ በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደሥራ ተገብቷል።
በእዚህም በአሁኑ ወቅት በክልሉ የከተማና ገጠር ወረዳዎች ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
"ባለፈው ወር በተከናወነ የገቢ ማሰባሰብ ሥራም ከቦንድ ሽያጭ ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል" ብለዋል።
የክልሉ ህዝብ ለሕዳሴው ግድብ ግንባታ በተለያየ መንግድ እያደረገ ያለውን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክሮ እንዲቀጥል አቶ ሄኖክ ጥሪ አቅርበዋል።