በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ21ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለምቷል

ደብረ ማርቆስ (ኢዜአ)ጥር 12/2015 በምስራቅ ጎጃም ዞን ከ21ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ መልማቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ ፈንታሁን ቸኮል ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በአገር ውስጥ ለመተካት የተደረገው እንቅስቃሴ በአርሶ አደሩ ላይ መነሳሳትን ፈጥሯል።

በዚህም በበጀት ዓመቱ ከ20 ሺህ 500 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ ለማልማት ታቅዶ በተደረገ እንቅስቃሴ እስካሁን ድረስ 21ሺህ 400 ሄክታር መሬት መልማቱን ገልጸዋል።

የበጋ ስንዴ ልማቱ በቀጣይም በአርሶ አደሩ እና በባለሃብቱ ትብብር ተጠናክሮ ስለሚቀጥል ተጨማሪ ሄክታር መሬት በስንዴ እንደሚሸፈንም አስታውቀዋል።

አቶ ፈንታሁን እንዳሉት ከ70 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ በሚካሄደው የበጋ ስንዴ ልማት ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል።

ከሚመረተው ስንዴ ውስጥ ከ190 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው መንግስት ወደ ውጭ ለመላክ የያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚውል ጠቁመው፣ "ቀሪው ለአገር ውስጥ ገበያና ለቤት ውስጥ ምግብ ፍጆታ ይውላል" ብለዋል።

"አርሶ አደሮቹ ባለፈው የመኸሩ ወቅት ያለሙትን ስንዴ በማንሳት ፈጥነው ወደበጋ ስንዴ ልማት እንዲገቡ በተደረገ ውይይት ለማልማት ከታቀደው ሄክታር በላይ መሬት ሊለማ ችሏል" ሲሉም ገልጸዋል።

መምሪያ ሃላፊው እንዳሉት መንግስት የመስኖ ስንዴ ልማቱን ለማሳካት በቂ የማዳበሪያና የግብአት አቅርቦት እንዲኖር አድርጓል።

ከእዚህ በተጨማሪ ከ6 ሺህ በላይ የውሃ መሳቢያ ጀኔሬተሮችን በግልና በቡድን ተደራሽ ማድረጉንም ነው የጠቆሙት።

በበጋ ስንዴ ልማቱ እየተሳተፉ ካሉ አርሶ አደሮች መካከል በአዋበል ወረዳ ጎደና ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙቀት አለነ በበኩላቸው፣ ከግማሽ ሄክታር በሚበልጥ ማሳ ላይ ስንዴ እያለሙ መሆኑን ገልጸዋል።

የዘሩት ስንዴ በአሁኑ ወቅት ቡቃያ ደረጃ ላይ መድረሱንና በቀጣይ አስፈላጊውን የሰብል እክብካቤ በማድረግ የተሻለ ምርት ለማግኘት ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

"ይሄን ያህል ጊዜ ስኖር ስንዴ በመስኖ ይለማል ብዬ አላስብም ነበር" ያሉት ደግሞ በማቻከል ወረዳ የየውላ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ይርጋዓለም ጫኔ ናቸው።

ከእዚህ ቀደም የተለያዩ የጓሮ አትክልቶችን በመስኖ እያለሙ ይጠቀሙ እንደነበር አስታውስው፣ ግማሽ ሄክታር በሚሆን ማሳ ላይ የዘሩት የስንዴ ቡቃያ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ይህም ለቀጣይ የምርት ዘመን ተጨማሪ መሬት ተከራይተው በበጋ ስንዴ ለማልማት እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል።

በምስራቅ ጎጃም ዞን ባፈው ዓመት ከ4ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ የመስኖ ስንዴ የተሸፈነ ሲሆን ከእዚህም ከ140 ሺህ ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ማግኘቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም