በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች ተፈጻሚነት አብረን እንሰራለን-የወዳጅ አገራት ፓርቲዎች መልእክት - ኢዜአ አማርኛ
በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባኤ ለሚተላለፉ ውሳኔዎች ተፈጻሚነት አብረን እንሰራለን-የወዳጅ አገራት ፓርቲዎች መልእክት
አዲስ አበባ መስከረም 23/2011 ኢትዮጵያ በ11ኛው የኢህአዴግ ጉባዔ በምታሳልፋቸው ቀጣይ አቅጣጫዎች አብረው እንደሚሰሩ የወዳጅ አገራት ፓርቲዎች ልዑካን ተናገሩ። የቻይና፣ ጀርመን፣ ሱዳን፣ ታንዛንያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳና ሌሎች አገራት ተወካዮች በሀዋሳ እየተካሄደ ባለው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ መልክት አስተላልፈዋል። የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ተወካይ ሚስተር ቦዬ ጁ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባርና የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ላለፉት 20 ዓመታት ሁለቱን አገራት ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ አብረው ሲሰሩ ቆይተዋል ሲሉ አውስተዋል። የሁለቱ አገራት ፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ጠቃሚ ፖለቲካዊ ግንኙነቶችን በመለዋወጥ ለአገራቱ እድገት አስተዋጽኦ አድርጓል ሲሉም አንስተዋል። የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ በቀጣይም ከኢህአዴግ ጋር ያለውን ግንኙነት በማጠናከር በቻይናና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ የልማት ግንኙነት በማጠናከር አብሮ ይሰራል ሲሉም አረጋግጠዋል። የጅቡቲ ገዥ ፓርቲ ተወካይ ሚስተር አሊ አብዲ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ዴሞክራሲያዊና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል ብለዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በኢትዮጵያና በቀጠናው ለሚያከናውናቸው ተግባራት ፓርቲያቸው አብሮ እንደሚሰራ ነው የገለጹት። የኬንያ ገዥ ፓርቲ ተወካይ ሚስተር አብሪሃም ሊሞ በበኩላቸው የኬንያ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በጉባኤው በሚያስተላልፋቸው አቅጣጫዎች መሰረት አብሮ ይሰራል። የደቡብ አፍሪካ ኤኤንሲ ፓርቲ ተወካይ አምባሳደር ፕሮፌሰር ኢክባል ጀዝባይ በኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ወራት እየታዩ ያሉ ለውጦችን በማድነቅ ንግግራቸውን ጀምረዋል። ተወካዩ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ሰላም በበጎ በማንሳት ኢትዮጵያ በቀጣይም በሰላምና በሌሎች የልማት ስራዎችም በምትሰራቸው ስራዎች ላይ ደቡብ አፍሪካ አብራ ትሰራለች ብለዋል። የቬትናም ኮሚኒስት ፓርቲ ተወካይ ሚስተር ኑጌን ዶንግ በበኩላቸው ፓርቲያቸው ለህዝቦች ብልጽግና ከኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ጋር ግንኙነቱን ታጠናክራለች ብለዋል። የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ተወካይ ሚስተር ኮንስታንቲን ኮን በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ልማቶችን ጀርመን ታደንቃለች ሲሉ ተደምጠዋል። የፖለቲካ ፓርቲ ብቻውን ችግሮችን ሊፈታ አይችልም ያሉት ተወካዩ፤ የህዝቦች ተሳትፎም ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል። ኢትዮጵያ ቀጣይ ለምታከናውናቸው የልማትና ሌሎች ስራዎች ጀርመን አጋርነቷን እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል። የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር ተወካይ ሚስተር ቲቶ ሪፋራ ፣የሱዳን ተወካይ ዶክተር ፋይሰል ሃሰንና የታንዛንያ ገዥ ተወካይም መልእክት አስተላልፈዋል። "አገራዊ አንድነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና" በሚል መሪ ሐሳብ በሃዋሳ እየተካኬደ ያለው 11ኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባኤ ከሰዓትም ቀጥሎ እየተካሄደ ነው።