የቻን ውድድር የስምንተኛ ቀን ውሎ

233

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 12/2015 በሰባተኛው የአፍሪካ አገራት ሻምፒዮና(ቻን) ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

በምድብ አራት ከምሽቱ 1 ሰአት አንጎላ ከሞሪታኒያ በሚሉድ ሀዴፊ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ሶስት አገራት ባሉበት ምድብ ሶስት አንጎላ ከማሊ ባደረገችው የመጀመሪያ ጨዋታ ሶስት አቻ መለያየቷ የሚታወስ ነው።በአንጻሩ ሞሪታኒያ በምድቧ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

በምድብ አምስት ኮንጎ ብራዛቪል ከኒጀር ከምሽቱ 4 ሰአት በሚሉድ ሀዴፊ ስታዲየም ጨዋታዋን ያደርጋሉ።

ሶስት አገራት በተደለደሉበት ምድብ አምስት ኮንጎ ብራዛቪል በመጀመሪያ የምድብ ጨዋታዋ በካሜሮን 1 ለ 0 ተሸንፋለች።ተጋጣሚዋ ኒጀር በምድቧ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች።

በሌላ በኩል ደግሞ ትናንት በምድብ ሶስት በተደረገ ጨዋታ ጋና ሱዳንን 3 ለ 1 አሸንፋለች።

ኮናዱ ይዶም፣ዳንኤል አፍሪዬ እና ሰይዱ ሱራጅ ለጥቋቁሮቹ ከዋክብቶች ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

ለሱዳን ብቸኛዋን ግብ አል ጎዞሊ ሁሴን ኖህ ሞሐመድ ከመረብ ላይ አሳርፏል።በዚህ ጨዋታ ለጋና ሁለተኛውን ግብ ያስቆጠረው ዳንኤል አፍሪዬ በ97ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

በምድብ ሶስት ሞሮኮ ራሷን ከውድድሩ ማግለሏን ተከትሎ ጋና፣ሱዳን እና ማዳጋስካር በተመሳሳይ የ3 ለ 0 እና የ3 ነጥብ የፎርፌ ውጤት አግኝተዋል።

በአልጄሪያ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው እና በአገር ውስጥ ሊግ የሚገኙ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት የቻን ውድድር እስከ ጥር 27 ቀን 2015 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም