ቀጥታ፡

የጥምቀት በዓል በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለፀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 11 / 2015 በሀገር አቀፍ ደረጃ የተከበረው የጥምቀት በዓል አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ገለፀ።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ ካስመዘገበቻቸው ከማይዳሰሱ ቅርሶች ውስጥ አንዱ የሆነው የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል ከሰላም ወዳዱ ሕዝብ ጋር በመተባበርና ባደረገው ቅንጅታዊ የፀጥታ ሥራ በዓሉ ያለ ምንም የፀጥታ ችግር በመላው ሀገራችን በሰላምና በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ማለፉን ገልጿል፡፡

ለዚህ ስኬት ከግብረ-ኃይሉ የተሰጠውን መግለጫ ከግምት ውስጥ በማስገባት በዓሉ በሰላም ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ላደረጋችሁ ዜጎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የበዓሉ አስተባባሪዎች፣ የእምነቱ ተከታዮች፣ እንዲሁም የሀገራችን ወጣቶች ለፀጥታ አስከባሪ አካላት ያሳያችሁት ከፍተኛ ትብብር ዓርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጿል።

በመሆኑ በነገው ዕለት የሚገቡ ታቦታትም እንደዛሬ ሁሉ በሰላም እንዲገቡ መላው ህብረተሰቡ ከፀጥታ አካላት ጋር እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ እያቀረበ እስከአሁን ለአደረጋችሁት ቀና ትብብር ላቅ ያለ ምስጋና አቅርቧል።

በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በሥራው ላይ የተሰማራችሁ የፀጥታና ደኅንነት አባላትም ከራሳችሁ በፊት የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት በማስቀደም የተሰጣችሁን ሀገራዊ ተልዕኮ ከህዝብ ጋር በመተባበር በብቃት በመወጣት የተፈለገውን ግብ በማሳካት ትልቁን ድርሻ ስለተወጣችሁ የጋራ ግብረ-ኃይሉ የላቀ ምስጋና አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም