በምንጃር ሸንኮራ የሚከበረው የኢራቡቲ የጥምቀት በዓል ለቱሪዝም መስህብ ለማዋል ይሰራል- የቱሪዝም ሚንስቴር

13

ደብረ ብርሃን ኢዜአ ጥር 11 ቀን 2015 ዓም. በምንጃር ሸንኮራ በየዓመቱ የሚከበረው የኢራቡቲ የከተራና ጥምቀት በዓል ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በማክበር ለቱሪስት መስህብነት ለማዋል እንደሚሰራ የቱሪዝም ሚንስቴር አስታወቀ።

የጥምቀት በዓል በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በአምሳለ ዮርዳኖስ በኢራንቡቲ ቀበሌ በሸንኮራ ወንዝ በድምቀት ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት ሚንስቴሩ የቱሪዝም ገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ እሸቱ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ እምቅ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሃብት ያላት ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ካሏት በርካታ የቱሪስት መስህብ ሃብቶች ውስጥ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው የጥምቀት በዓል አንዱ መሆኑን አስታውሰዋል።

ዳይሬክተሩ አቶ ንጉሴ አክለውም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጭ ጎብኞችን እየሳበ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም በምንጃር ሸንኮራ የሚከበረውን የኢራንቡቲ ቀበሌ የጥምቀት በዓል ከመልክዓ ምድሩና ከህብረተሰቡ የአኗኗር ባህል ጋር አስተሳስሮ በማልማትና በማስተዋወቅ ለገቢ ምንጭነት ማዋል ይገባል ብለዋል።

የቱሪዝም ሚንስቴርም በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም ፀጋ በማጥናት በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪስት መስህብ ለማድረግ ድርሻ እንደሚወጣ አስታውቀዋል።

በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽህፈት ቤት የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያና የሰሜን ሸዋ ሀገረ ሰብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ እንደሉት የጥምቀት በዓል በምንጃር ሸንኮራ ከሁሉም የተለየ ነው።

በወረዳው ኢራቡቲ ቀበሌ ላይ 44 ታቦታት በአንድ ላይ ወንዝ ዳርቻ ወርደው በማደር ዛሬ በሰላም ተመልሰው ወደእየ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው የተመለሱበት መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል።

የወረዳው ህዝብም በፍቅር በመረዳዳትና በመተሳሰብ በዓሉን በጋራ ከከተራው ጀምሮ በድምቀት እክብሮ ታቦታቱን ወደ ነበሩበት በመመለስ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ እንግዶችንና ቱሪስቶችን ምግብና ምኝታ በማዘጋጀት በኢትዮጵያዊ ጨዋነት ማስተናገዱ አካባቢው ለመስህብ ተመራጭ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በበኩላቸው ባለፉት ሶሰት ዓመታት የነበረው ሀገራዊ ችግር ዜጎች በነፃነት በዓላቸውን እንዳያከብሩ እንቅፋት ፈጥሮ ነበር አስታውሰዋል።

"ከፈጣሪ በተሰጠን የእርቅ ፀጋ ሰላማችን ተመልሶ ፊታችነን ወደ ልማት የመለስንበት ወቅት ላይ በመሆናችን ጥምቀትን በሰላም ለማክበር መብቃታችን አስደሳች" ነው ብለዋል።

የተገኘው ሰላምም በዞኑ በጥናት የተለዩ 149 የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማትና በማስተዋወቅ የቱሪዝም ዘርፉን ለስራ እድል ፈጠራና ለኢንቨስትመንት ለማዋል የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።

ጥምቀትን ለማክበር ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር የመጡ ምእመናን በዓሉንና አካባቢውን በማስተዋወቅ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ፍሰት እንዲጨምር የድርሻቸውን እንድትወጡ አሳስበዋል።

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በተከበረው የጥምቀት በዓል ከ18 አድባራት የተውጣጡ 44 ታቦታት ከጊዜያዊ ማረፊያቸው ተነስተው በሰለም ወደ መጡበት አብያተ ከርስቲያን መመለሳቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም