የጥምቀት በዓልን በኢትዮጵያ በማክበራችን ደስ ብሎናል፤ በአሉንም የማስተዋወቅ ስራ እንሰራለን -የውጭ ሀገራት ዜጎች - ኢዜአ አማርኛ
የጥምቀት በዓልን በኢትዮጵያ በማክበራችን ደስ ብሎናል፤ በአሉንም የማስተዋወቅ ስራ እንሰራለን -የውጭ ሀገራት ዜጎች
አርባ ምንጭ ጥር 11/2015 (ኢዜአ) በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበውን የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ በማክበራችን ተደስተናል፤ በአሉንም የማስተዋወቅ ስራ እንሰራለን ሲሉ የውጭ ሀገራት ዜጎች ገለጹ፡፡
በበዓሉ ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገት ጉልህ ድርሻ እንዳለው በበአሉ ላይ የታደሙ የውጭ ሀገራት ዜጎች ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
ከእስራኤል መጥተው በአርባ ምንጭ ከተማ በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ የታደሙት ኦማ አፌይ "በኢትዮጵያ በየዓመቱ ጥር ወር የሚከበረው የጥምቀት በዓል ልዩ ድባብ ያለው በመሆኑ ከባለቤቴ ጋር በመሆን በዓሉን ለማክበርና ለመጎብኘት መጥቻለሁ" ብለዋል፡፡
እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር የረዥም ጊዜ ወዳጅነት ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው "ወንድማማቾች እንደመሆናችን መጠን ወዳጅነታችንም እንደዚሁ ተጠብቆ ይቀጥላል" ብለዋል፡፡
"የኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ምእመናን በአንድ ላይ በባህላዊና ሃይማኖታዊ ትውፊቶች በዓሉን ሲያከብሩ መመልከት እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው" ብለዋል ፡፡
"ወደ ሀገሬ ስመለስ ጓደኞቼና ወዳጆቼ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ጥር ወር በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ እንዲታደሙና እንዲጎበኙ የማስተዋወቅ ስራ እሰራለሁ" ሲሉ አክለዋል ፡፡
ሌላው ከእስራኤል የመጡት ዮሲ ኢብራሂም በበኩላቸው "ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሰላም እንደሌለ ብሰማም በአካል መጥቼ ሁኔታዎችን ስመለከት ፍጹም የተረጋጋ ሰላምና ጸጥታ መኖሩን በማየቴ ደስ ብሎኛል" ብለዋል፡፡
የኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ስነስርአትን ከከተራ ጀምሮ መከታተላቸውን ጠቅሰው በአሉ ደግሞ ደማቅና ሰላማዊ በሆነ መልኩ በመከናወኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል ።
የጥምቀት በዓል በዓለም በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ ትልቅ ሀብት በመሆኑ ስርአቱን በኢትዮጵያ መጥቶ መመልከት መንፈስን ያድሳል" ብለዋል፡፡
የጥምቀት በዓል በዓለም ልዩ ድባብ ያለው ሃይማኖታዊ በዓል በመሆኑ ለቱርዝም ዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው የተናገሩት ደግሞ ከቼክ ሪፐብሊክ የመጡት ዶክተር ካሬል ማርቲኔክ በጥምቀት በዓል ላይ መታደም በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ በኢትዮጵያ መጥተው የጥምቀት በዓልን ማክበራቸውን አስታውሰው "ዘንድሮ ለሶስተኛ ጊዜ በማክበሬ ደስ ብሎኛል " ሲሉ አክለዋል ፡፡
በዓሉ እንደሀገርና ዓለም የቱሪዝም መናገሻ መሆኑን ዶክተር ካሬል ተናግረዋል፡፡