ኢህአዴግ በ11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤው የግንባሩን አባላት ዴሞክራሲያዊ አንድነት ያሳድጋል...ነባር የህወሃት ታጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
ኢህአዴግ በ11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤው የግንባሩን አባላት ዴሞክራሲያዊ አንድነት ያሳድጋል...ነባር የህወሃት ታጋዮች
ሽሬ እንዳስላሴ መስከረም 23/2011 የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር/ኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የግንባሩን አባላት ዴሞክራሲያዊ አንድነት ያጠናክራል ብለው እንደሚጠብቁ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነባር ታጋዮች ገለጹ። ነባር የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ/ህወሃት ታጋዮች እንደገለጹት ጉባኤው በእህት ድርጅቶች የሚስተዋለውን የቅንጅት ችግር በመፍታት ግንባሩን ወደ ተሻለ አቅጣጫ ይመራዋል። በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ የሚኖሩት ነባር የህወሓት ታጋይ ፍስሓ አባዲ “በግንባሩ እህት ድርጅቶች እየተስተዋለ ያለውን የቅንጅት ክፍተት የሚሞላ ውሳኔ ግንባሩ ያስተላለፋል ብዬ እጠብቃለሁ” ብለዋል። እንዲሁም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን እየተስተዋለ ያለውን ስርዓት አልበኝነት መልክ ለማስያዝ የሚያስችሉ ውሳኔዎች እንደሚያስተላልፍ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል። “አሁን ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው” ያሉት ደግሞ ተጋይ ግደይ ኪዳኔ ናቸው። ይህን በውጥረት የተሞላ እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስና ዘላቂ ሰላምን ለማስፍን የሚያስችሉ ውሳኔዎች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል። “ኢህአዴግ ለህገ-መንግስቱ መከበር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጡ ውሳኔዎች እጠብቃለሁ”ያሉት ደግሞ ነባር ታጋይ አርአያ በላይ ናቸው። “ማንኛውም ዜጋ በፈለገበት ክልል ተንቀሳቅሶ ኑሮውን ለማሻሻል የሚያስችለው ህገ-መንግስታዊ መብቱ ሳይሸራረፍ እውን እንዲሆን ከጉባኤው ብዙ ይጠበቃል” ብለዋል። ዛሬ ከተጀመረው የኢህአዴግ 11ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ የኢትዮጵያን መጻኢ እድል ብሩህ የሚያደርጉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት እንደሚሆን አስተያይት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።